በቻይናዋ ውሃን ከተማ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ እገዳ ተነስቶ ህይወት እንደገና ቀጥሏል
በቻይናዋ ውሃን ከተማ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ እገዳ ተነሳ
ለ2 ወር ከ15 ቀናት ያህል በሯን ዘግታ የከረመችው የቻይናዋ ውሃን ከተማ በሯን ከፍታለች፡፡
ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ እገዳ አንስታም ዜጎቿ ከእኩለ ሌሊት ወዲህ ልክ እንደወትሮው መንቀሳቀስ ተራርቀው የነበሩ ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ መገናኘት ጀምረዋል፡፡
ይህንኑ ምክንያት በማድረግም ነዋሪዎች ደስታቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል፡፡ ከተማዋም በመብራቶች ተንቆጥቁጣ ነው ያመሸችው፡፡
11 ሚሊዬን ነዋሪዎች ያሏት የሁቤይ ክልል ርዕሰ ከተማዋ ውሃን መላው ዓለምን በማዳረስ ላይ ያለው እና የብዙዎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የኮሮና ወረርሽኝ መነሻ ተደርጋ ትጠቀሳለች፡፡በርካታ ነዋሪዎቿንም አጥታለች፡፡
ከውሃን የተነሳው ቫይረስ ያዳረሳት ቻይናም ከ3 ሺ 3 መቶ በላይ ዜጎቿን ገብራ አሁን ማንሰራራት ጀምራለች፡፡ቫይረሱን ከመቆጣጠር አልፋ ሌሎች በቫይረሱ እየተፈተኑ ያሉ ሃገራትን በመደገፍ ላይ ትገኛለች፡፡
ውሃን የጣለችውን የእንቅስቃሴ እገዳ ብታነሳም የሁቤይ አስተዳደር ግን አሁንም ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል የመጀመሪያ ደረጃ ጥንቃቄ እንደሚቆይ አስታውቋል፡፡ በአስተዳደሩ የሚገኙ የትምህርትና ተቋማት ተዘግተው እንደሚቆዩም ተገልጿል፡፡
በውሃንም ቢሆን አሁንም ጥንቃቄ ሊለይ እንደማይገባ ነው የከተማይቱ ባለስልጣናት የሚያሳስቡት፡፡