የቻይና እና ሩሲያ መሪዎች በኡዝቤኪስታን ሊገናኙ ነው ተባለ
የመሪዎቹ መገናኘት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዓለም ፊቱ ላዞረባት ሞስኮ ትልቅ ፋይዳ አለው ተብሏል
ሞስኮና ቤጂንግ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባላቸው ግንኙነት የተነሳ የቅርብ አጋሮች ሆነው ብቅ ብለዋል
የቻይና እና ሩሲያ መሪዎች በቀጣይ ሳምንት በኡዝቤኪስታን እንደሚገናኙ ተገለጸ፡፡
በቤጂንግ የሩሲያ ተወካይ አንድሬ ዴኒሶቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን በሚቀጥለው ሳምንት መስከረም 15 ቀን፤2022 ይገኛሉ፡፡
መሪዎቹ በኡዝቤኪስታን ከሚካሄደው የሻንጋይ የትብብር ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ተገናኝተው የጎንዮሽ ውይይት የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳለቸው የሚነገርላቸው መሪዎቹ በኡዝቤኪስታን ፊት ለፊት ሲገናኙ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ የመጀመሪያ እንደሚሆንም የሩሲያው የዜና ወኪል /ታስ/ ዘግቧል፡፡
በተለይም በኮሮና ምክንያት ኩፉኛ የተፈተነችው ሀገር መሪ ለሆኑት ለቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ የመጀመሪያ የባህር ማዶ ጉዞ መሆኑ ነው፡፡
የመሪዎቹ መገናኘት ፤ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ዓለም ፊቱ ላዞረባት ሞስኮ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው እየተገለጸ ነው፡፡
ሞስኮ እና ቤጂንግ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባለቸው ግንኙነት የቅርብ አጋሮች ሆነው ብቅ ያሉበት አጋጣሚ ተፈጥረዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከመጀመሯ በፊት በሀገራቱ መካከል የተደረሰው የ”ገደብ የለሽ” ትብብር ስምምነት እንዲሁም ከመዘቻው በኋላ ዓለም በአንድ ድምጽ ሩሲያን ሲያወግዝ የቤጂንግ ዝምታን መምረጥ፤ በቤጂንጋና ሞስኮ የተፈጠረው የአጋርነት መንፈስ የሚያመለክቱ ስለመሆናቸው ይነሳል፡፡
መሪዎቹ በቅርቡ የቤጅንግ እና ሞስኮን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የቪዲዮ ውይይት ማድረጋቸውን አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቶቹ በነበራቸው ውይይት ቻይና ሩሲያ ከ 20 ዓመት በፊት የተተፈራረሙት የመልካም ጉርብትናና የወዳጅነት ትብብር እንዲቀጥል መስማማታቸውንም ነበር ሲጂቲኤን በወቅቱ የዘገበው፡፡
የሞስኮ እና የቤጅንግ ትብብር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አወንታዊ ሃይል እንደሆነም በውይይቱ ይፋ ሆነዋል፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት የሰው ልጅ በርካታ ችግሮች እየገጠሙት ባለበት በዚህ ወቅት የሁለቱ ሀገራት ትብብር ለዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ ምሳሌ ይሆናል ማለታቸውም ይታወሳል፡፡