የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከ60 ሺህ በላይ ሰራተኞችን በመቀነስ ከገጠማቸው ችግር ለመውጣት ጥረት እያደረጉ ነው
በፈረንጆቹ 1994 የተቋቋመው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያሆ ከ20 በመቶ በላይ ሰራተኞቹን በቀጣዩ ሳምንት ሊያሰናብት መሆኑን አስታውቋል።
በዚህ ውሳኔውም ከ1 ሺህ በላይ ሰራተኞች ተጠቂ ይሆናሉ ተብሏል።
ያሆ የማስታወቂያ ስራዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ አዲስ መዋቅራዊ አሰራር ለመተግበር በማለም ነው ውሳኔውን ያሳለፈው።
“ውሳኔው ቀላል አይደለም፤ ነገር ግን በማስታወቂያው ዘርፍ ለማድረግ ላሰብነው ማሻሻያና ለደንበኞቻችን የተሻለ አገልግሎት ለማቅረድ ውሳኔው ማሳለፋችን ግድ ነው” ብለዋል የኩባንያው ቃል አቀባይ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
ያሆ በ2021 በ5 ቢሊየን ዶላር ለኦፖሎ ግሎባል ማኔጅመንት ከተሸጠ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን በማስታወቂያ ስራ ላይ አድርጓል።
ኩባንያው “ያሆ አድቨርታይዚንግ” የሚል አዲስ የስራ ክፍል በመፍጠር ከጎግልና ፌስቡክ የገጠመውን ፉክክር ለመቀልበስ ማቀዱ ተገልጿል።
ተንታኞች ግን የቴክኖሎጂ ቀንዲሉ ያሆ ዘመኑን የዋጁ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ወደ ስራ ካላስገባ በያዘው አካሄድ ገበያው ላይ ተፎካካሪ ሆኖ መቀጠል እንደሚከብደው ይናገራሉ።
በቀን ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰዎችን የሚያስተናግደው ያሆ፥ በበይነ መረብ መልዕክት መለዋወጥን ያስጀመረ የአሜሪካ ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል።
ዜናዎችን፣ የስፖርትና የፋይናንስ መረጃዎችን ማጋራት በመጀመር እና ሙዚቃን በኦንላይን ማዳመጥን በማስተዋወቅም ፈር ቀዳጅ ነው።
የኦንላይን ማስታወቂያዎችን በመልቀቅ ገቢ በማስገባት ቀዳሚ የሆነው የቴክኖሎጂ ኩባንያ በበርካታ ጉዳዮች ፊታውራሪ ቢሆንም መስመሩን የተከተሉትን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፉክክር መቋቋም እየተሳነው መምጣቱ ይነገራል።
አዲሱ የሰራተኞች ቅነሳ ውሳኔውም ወጪውን በመቀነስ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ያሆ አድቨርታይዚንግ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ ተገልጿል።
ከያሆ አስቀድሞ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ጎግል፣ ማይክሮሶፍትን ጨምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከ60 ሺህ በላይ ሰራተኞቻቸውን ማሰናበታቸው ይታወሳል።