የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ሄቦ” እየተከበረ ነው
የበዓሉ የመጀመሪያ ዕለት “ካማ ኬሳ” ይባላል
በዓሉ ከመስከረም 14 ቀን ጀምሮ በመከበር ላይ ነው
በደቡብ ክልል የየም ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ሄቦ” እየተከበረ ነው፡፡
በዓሉ ከመስከረም 14 ቀን ጀምሮ በመከበር ላይ ሲሆን የበዓሉ የመጀመሪያ ዕለት “ካማ ኬሳ” ይባላል፡፡
ቀኑ በቤተሰብ ውስጥም ሆነ በዘመድ አዝማድ መካከል የተፈጠረ ቅራኔና የሰነበተ ቂም ካለ በሽማግሌዎች አማካይነት ሰላም ወርዶ እርቅ የሚፈፀምበት ነው፡፡
“ካማ ኬሳ” በዋናነት ቂምና ቁርሾን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት ላለመሻገር ሲባል እንደሚፈጸምም ነው የሚገለጸው፡፡
ቂምና ቁርሾን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሻገሩ ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሊዳርግ እንደሚችልም በብሔረሰቡ አባላት ይታመናል፡፡
“ሄቦ”በብሔረሰቡ ከሚከበሩ በዓላት አንዱ ሲሆን መቼ መከበር እንደጀመረ የሚያሳዩ መረጃዎች የሉም፡፡ ሆኖም ከጥንት ጀምሮ ይከበር እንደነበር የብሔረሰቡ ተወላጆች ይናገራሉ፡፡
ለ“ሄቦ” አባዎራዎች፣ እማዎራዎች እና ወጣቶች ዕድር በመግባትና ዕቁብ በመጣል ለረዥም ጊዜ (የዓመት) ይቆጥባሉ፡፡
ቁጠባው ዕርድን ጨምሮ የአልባሳት ወጪን ለመሸፈን የሚውል ነው እንደ ብሔረሰብ አባላቱ ገለጻ፡፡
የማ ኡሻ ወይም ቺፋ (ቦርዴ) የሚባል መጠጥ በበዓሉ የተለመደ ነው፡፡ መጠጡ ከገብስ እና ቀይ ጤፍ ነው የሚዘጋጀው፡፡ የመጠጡ የዝግጅት ጊዜ ከጥር ወር እንደሚጀመርም ይነገራል፡፡