ከየመን የተተኮስ ክሩዝ ሚሳኤል የኖርዌይ እቃ ጫኝ መርከብን አቃጠለ
አሜሪካ በባብ አል ማንደብ በደረሰው ጥቃት መርከቧ በእሳት ብትያያዝም በመርከበኞቹ ላይ ጉዳት አልደረሰም ብላለች
የሃውቲ ታጣቂዎች የኖርዌይ ሰንደቅ አለማ በምታውለበልበው መርበብ ላይ ለደረሰው ጥቃት ሃላፊነት አልወሰዱም
በየመን የሃውቲ ታጣቂዎች ከተቆጣጠሩት አካባቢ የተተኮስ ክሩዝ ሚሳኤል እቃ ጫኝ መርከብን መምታቱን የአሜሪካ ጦር አስታውቋል።
ከባብ አል ማንደብ በስተሰሜን 111 ኪሎሜትር ላይ የደረሰው ጥቃት መርከቧን በእሳት አያይዟታል ተብሏል።
የኖርዌይን ሰንደቅ አላማ የምታውለበልበው መርከብ ጉዳት ቢደርስባትም በመርከበኞቹ ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ግን የአሜሪካ ጦር መግለጫ ያሳያል።
ጥቃቱ ሲደርስ ምንም አይነት የአሜሪካ መርከብ በቀይ ባህር ጉዞ እያደረገ አልነበረም ያለው የአሜሪካ ጦር፥ ጥቃት ለደረሰባት መርከብ የድረሱልኝ ጥሪ በአካባቢው ያለች የአሜሪካ መርከብ ምላሽ መስጠቷን አብራርቷል።
የአትክልት ዘይት እና ባዮፊዩል የጫነችው መርከብ ከማሌዥያ ወደ ጣሊያን ጉዞ እያደረገች ነበር ተብሏል።
ጥቃቱ ሀውቲዎች ከሚቆጣጠሩት አካባቢ መሰንዘሩን ዋሽንግተን ብትገልጽም ቡድኑ እስካሁን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አልገለጸም።
በኢራን የሚደገፉት የሃውቲ ታጣቂዎች እስራኤል በሃማስ ላይ ጥቃት ማድረስ ከጀመረች ጀምሮ በቀይ ባህር የእስራኤል መርከቦች ዝር እንዳይሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ባለፈው ቅዳሜም የትኛውንም ወደ እስራኤል የሚያቀና መርከብ በሚሳኤል እንመታለን ሲል መዛቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
የየትኛውም ሃገር ንብረት የሆኑ መርከቦች ወደ እስራኤል ከማቅናት እንዲታቀቡ ባስጠነቀቀ ማግስትም የኖርዌይ ኩባንያ ንብረት የሆነች መርከብን በክሩዝ ሚሳኤል መቷል፤ ምንም እንኳን እስካሁን ማረጋገጫ ባይሰጥም።
ባለፈው ወር የብሪታንያ ንብረት የሆነች መርከብን ያገቱት የሃውቲ ታጣቂዎች እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ካላቆመች ጥቃታችን ይቀጥላል ብለዋል።
የሃውቲን ጥቃቶች ያወገዙት አሜሪካ እና ብሪታንያ ከጥቃቱ ጀርባ አለች ያሏትን ኢራን ኮንነዋል።
ቴህራን በበኩሏ ሃውቲዎች የሚወስዱት እርምጃ በራሳቸው ውሳኔ የሚፈጸም ነው በሚል ወቀሳውን ውድቅ አድርገዋል።
ሳኡዲ አረቢያ በበኩሏ አሜሪካ በቀይ ባህር ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የምትወስደው አጻፋዊ ምላሽ ቀጠናውን ይበልጥ እንዳያተራምሰው ጥንቃቄ እንድታደርግ እየጠየቀች ነው።