በቦምብ ከተደበደቡ ቦታዎች መካከል በቀይ ባህር ላይ ያሉ መርከቦችን ከርቀት መምታት የሚያስችሉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ይገኙበታል ተብሏል
የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን ለአሜሪካ ጥቃት ምላሽ እንደሚሰጥ ዛተ፡፡
አንድ ዓመት ያለፈው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በሰላም ስምምነት ይጠናቀቃል ቢባልም አድማሱን እያሰፋ ይገኛል፡፡
የእስራኤል ጦር ከሐማስ ታጣቂዎች ባለፈ ከሊባኖሱ ሂዝቦላህ ጋር የመሬት እና የአየር ላይ ውጊያዎችን በማድረግ ላይ ሲሆን የየመኑ ሁቲ አማጺ ቡድን እስራኤልን በማጥቃት ላይ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለእስራኤል ድጋፍ ያደርጋሉ ከሚባሉ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ በሆነችው አሜሪካ ላይም ጥቃት እያደረሰ ይገኛል፡፡
የአሜሪካ አየር ሀይል በዛሬው ዕለት የሁቲ አማጺያን ይዞታዎች እና ጦር መሳሪያ ማከማቻ ቦታዎች ላይ በከባድ ቦምብ ድብደባ ፈጽሟል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ የሁቲ አማጺ ቡድን አሜሪካ ለደረሰችበት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ዝቷል፡፡
በኢራን እንደሚደገፍ የገለጸው የሁቲ አማጺ ቡድን የፖለቲካ ክንፍ ቢሮ እንዳለው የአሜሪካ ጥቃት ምላሽ የሚያሰጥ ነው ማለቱን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሊዮልድ ኦስቲን እንዳሉት የመሬት ውስጥ ኢላማዎችን መምታት በሚያስችለው ቢ2 በተሰኘው ከባድ ቦምብ በዋና ዋና የሁቲ አማጺ ቡድን ላይ ድብደባ ተፈጽሟል ብልዋል፡፡
ግብጽ በቀይ ባህር ንግድ መቀዛቀዝ ምክንያት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷን ገለጸች
በድብደባው ስለደረሰው የጉዳት መጠን እስካሁን በሁለቱም ወገኖች ያልተገለጸ ሲሆን አሜሪካ ግን የጉዳት መጠን ጥናቶችን እያካሄደች መሆኗን አስታውቃለች፡፡
የሁቲ አማጺያን ካሳለፍነው ጥቅምት ወር ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ በሚሰነዝራቸው ጥቃቶች የንግድ መስመሩ ክፉኛ ተቀዛቅዟል፡፡
አማጺ ቡድኑ በተለይም ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሰንዝሯል፡፡