ሃውቲ ወደ እስራኤል መዲና የተኮሰው "ፍልስጤም 2" የተሰኘውን ባለስቲክ ሚሳኤል መሆኑን አስታውቋል
ከየመን የተተኮሰ ሚሳኤል ዛሬ ጠዋት በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ መውደቁ ተነግሯል።
የእስራኤል ጦር የአየር መቃወሚያ ስርአቱ ሚሳኤሉን መትቶ አለመቻሉንና በጥቂቱ 14 ሰዎች ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ የሚሳኤል ጥቃቱን ቡድኑ እንደፈጸመው ተናግረዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ጃፋ በተባለው የቴል አቪቭ መንደር የወደቀው ሚሳኤል "ፍልስጤም 2" የተሰኘው ሀይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል መሆኑንም አብራርተዋል።
"ሚሳኤሉ ትክክለኛ ኢላማውን መትቷል፤ (የእስራኤል) የአየር መቃወሚያ ስርአትንም ጥሶ አልፏል" ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ጥቃቱ "በጋዛ ለሚጨፈጨፉ ወንድሞቻችን አጋርነታችን ለማሳየት" የተፈጸመ ነው ብለዋል።
ሃውቲዎች የዛሬውን የሚሳኤል ጥቃት የፈጸሙት እስራኤል ከሁለት ቀናት በፊት በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት ከፈጸመችና በጥቂቱ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ካለፈ በኋላ ነው።
በ14 ጄቶች የተፈጸመው ድብደባ በሆዴይዳህ ወደብ እና ሰንአ የሚገኙ የሃውቲ መሰረተ ልማቶች፣ የሳሊፍ እና ራስ ኢሳ የነዳጅ ማከማቻዎች ላይ ኢላማ ያደረገ ነበር።
እስራኤል ለዛሬው የሃውቲዎች ጥቃት ምን አይነት ምላሽ እንደምትሰጥ ይፋ ባታደርግም የተጠናከረ የአየር ድብደባ እንደምታካሂድ ይጠበቃል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ፥ "ሃውቲዎች በእስራኤል ላይ እጁን የሚሰነዝር እጁ እንደሚቆረጥ ሁሌም ማስታወስ አለባቸው፤ እኛን የሚጎዳ በብዙ እጥፍ የእጁን ያገኛል" ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የየመኑ ቡድን የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከ200 በላይ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል በመተኮስ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን አሳይቷል። በቀይ ባህር የሚጓዙና ከእስራኤልና አሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይም ተደጋጋሚ ጥቃት አድርሷል።
አሜሪካ አጋሮቿን አስተባብራ በየመን ተከታታይ የአየር ጥቃት ብታደርስም ቡድኑ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን መተኮሱን አላቆመም።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሃውቲዎች ባለፈው ሳምንት ወደ እስራኤል ሚሳኤል ከተኮሱ በኋላ "በኢራን በሚደገፉ ሃይሎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ ዝተዋል።
እስራኤል በጋዛ በሃማስ፤ በሊባኖስ ደግሞ በሄዝቦላህ ላይ ጦርነት ማወጇ ይታወሳል፤ ሁለቱም ቡድኖች ከቴህራን የፋይናንስና የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያገኙ ይነገራል። እስራኤል የሄዝቦላህን ዋና ዋና አመራሮች ከገደለች በኋላ ባለፈው ወር የተኩስ አቁም ስምምነት ደርሳለች።
"ሃማስ ካልተደመሰሰ የጋዛው ጦርነት አይቆምም" ሲሉ የከረሙት ኔታንያሁ፥ ትራምፕ ዳግም ዋይትሃውስ ከመዝለቃቸው በፊት ተኩስ ለማቆም ድርድር እያደረጉ ነው ተብሏል።