የየመን ሂቲ አማጺ ቡድኖች የብሪታንያ መርከቦችን ማስመጣችንን እንቀጥላለን አሉ
አማጹ ቡድኖቹ ንብረትነቱ የብሪታንያ የሆነ መርከብን በቀይ ባህር ማስመጣቸው ይታወሳል
የየመን አማጺ ቡድኖች ከፍልስጤማዊያን ጎን ነን በሚል ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን እያጠቁ ይገኛሉ
የየመን ሂቲ አማጺ ቡድኖች የብሪታንያ መርከቦችን ማስመጣችንን እንቀጥላለን አሉ፡፡
ከስድስት ወር በፊት ለፍልስጤማዊያን ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡
ለ30 ሺህ ፍልስጤማዊያን ግድያ ምክንያት በሆነው በዚሕ ጦርነት የሚሳተፉ አካላት ቀስ በቀስ እየሰፉ እና ጉዳቱም እየጨመረ የመጣ ሲሆን የየመን ሁቲ አማጺያን ዋነኞቹ ናቸው፡፡
አሜሪካ እስራኤል ከመደገፍ እንድትታቀብ እና እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ጫና ለመፍጠር የተጀመረው የሁቲ አማጺ ቡድን ጥቃት እንዲቆም አሜሪካ እና አውሮፓ የባህር ሀይላቸውን ወደ ቀይ ባህር ቢልኩም አማጺያኑ ግን አሁንም ጥቃታቸውን ገፍተውበታል፡፡
በትናንትናው ዕለትም ንብረትነቱ የብሪታንያ የሆነ የንግድ መርከብ በሁቲ አማጺያን በደረሰበት የድሮን ጥቃት ምክንያት ሰምጧል፡፡
በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት እነዚህ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ንኪኪ አላቸው የተባሉ መርከቦችን ማስመጣችንን እንቀጥላለን ሲሉ መዛታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ አሜሪካ የብሪታንያ ንግድ መርከብ በደረሰበት የድሮን ጥቃት መስመጡን አረጋግጣለችም ተብሏል፡፡
እስራኤል ከሐማስ ጋር በጋዛ ለስድስት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማቷ የተገለጸ ሲሆን ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን ለመፈራረም ወደ ካይሮ ማምራታቸው ተገልጿል፡፡
የእስራኤል ሐማስ ጦርነትን ተከትሎ በቀይ ባህር በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የዓለም ንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ የተስተጓጎለ ሲሆን ግብጽ ከስዊዝ ካናል የምታገኘው ገቢም በግማሽ እንደቀነሰባት ተገልጿል፡፡
በአሜሪካ አስተባባሪነት ብሪታንያ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ የባህር ሀይላቸውን ወደ ቀይ ባህር በመላክ በሁቲ እና ይዞታዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ ናቸው፡፡