አሜሪካና ብሪታንያ በየመን ከ400 በላይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል - ሃውቲ
ሀገራቱ በሆዴይዳህ የሚፈጽሙትን ጥቃት በመጨመር ለፍልስጤማውያን አጋር እንዳንሆን ማስፈራራታቸውን ቀጥለዋል ብለዋል የሃውቲ ቃል አቀባይ
የየመኑ ቡድን ከእስራኤል፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ከ30 በላይ ጥቃቶችን መፈጸሙ ይታወሳል
አሜሪካና ብሪታንያ በየመን ከ400 በላይ የአየር ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የሃውቲ ታጣቂ ቡድን ገለጸ።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ዳይፋላህ አል ሻሚ ከሳባ ኒውስ ኤጀንሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ሀገራቱ ከጥር ወር ወዲህ 403 ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ከጥቃቶቹ ውስጥ 203ቱ በአውሮፕላን የተፈጸሙ መሆናቸውን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፥ ባለፈው ሳምንት ብቻ 86 ጥቃቶች መፈጸማቸውን አብራርተዋል።
በአየር ድብደባዎቹና ከጦር መርከቦች ላይ በተቃጡት ጥቃቶች በቡድኑ ይዞታዎች እና ተዋጊዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን ቃልአቀባዩ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የአሜሪካ እና ብሪታንያ ጥቃት አላማ የመን በፍልስጤም ጉዳይ የያዘችውን ጠንካራ አቋም በማስፈራራት ለማስለወጥ ነው ያሉት አል ሻሚ፥ ይህ ጥረታቸው ግን እንደማይሳካ አሳይተናቸዋል ብለዋል።
ሚሊየኖች በሰንአ እና በሌሎች ከተሞች አደባባይ በመውጣት የእስራኤልና አጋሮቿን ድርጊት መቃወማቸውን በማንሳትም “ለፍልስጤማውያን ያለን አጋርነት እስራኤልን በማውገዝ ብቻ የሚቆም እንዳልሆነ በተግባር ታይቷል” ነው ያሉት።
የሃውቲ ታጣቂ ቡድን የእስራኤልም ሆኑ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች በቀይ ባህር እንዳያልፉ ለማድረግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤት ማሳየታቸውንም አብራርተዋል።
አሜሪካ እና ብሪታንያ በሃውቲዎች ለተነሳው በየመን ከ400 በላይ ጥቃት ፈጽመዋል ክስ እስካሁን ምላሽ ባይሰጡም በሆዴይዳህ ወደብ አካባቢ ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም ላይ መሆናቸው ተዘግቧል።
ዋሽንግተን እና ለንደን የቀይ ባህር ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚል አጋሮቻቸውን በማስተባበር የጋራ የቅኝት ግብረሃይል ካሰማሩ በኋላ የንግድ መስመሩ መረጋጋት እየታየበት መሆኑን ይገልጻሉ።
በየመን የሃውቲ ይዞታዎችን በመደብደብ አቅሙን የማዳከሙን ስራም ተያይዘውታል።
በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ከ30 በላይ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃት የፈጸሙት ሃውቲዎች ግን የአሜሪካና ብሪታንያ ዜጎች የመንን ለቀው እንዲወጡ ከማሳሰብ ባሻገር የሀገራቱ መርከቦች ኢላማዎቻችን ናቸው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
29 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን የተገደሉበት ጦርነት ካልቆመም ጥቃታቸውን እንደሚቀጥሉ መዛታቸውን የሬውተርስ ዘገባ አስታውሷል።