በጎ አድራጊ ወጣቶች ዛሬ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች መንገደኞችን እጅ አስታጥበዋል
ለወገን ጤና መጠበቅ የሚታትሩት ወጣቶች
ኮሮና ቫይረስ የደቀነው ማህበረሰባዊ እና ሃገራዊ ስጋት ያሳሰባቸው የቪዥን ብራይት ኢትዮጵያ የወጣቶች የበጎ አድራጎት ማህበር አባላት ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ጎዳናዎች ጎራ ብለው መንገደኞችን ሲያስታጥቡ አርፍደዋል፡፡
በርከት ያሉ የማህበሩ አባላትም ውሃ እና ሳሙና (“ሳኒታይዘር”) በማቅረብም በርካታ መንገደኞችን በመገናኛ እና ፒያሳ አካባቢዎች አስታጥበዋል፡፡
“ ማስታጠቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ማህበረሰቡን ይበልጥ ለማንቃት ነው” የሚለው የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ ወጣ ሞቲ ቦረዳ በራሳቸው በማህበሩ አባላት ተነሳሽነትና ወጪ የተጀመረ መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል፡፡
ወጣቶቹ አገልግሎቱን በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች የማዳረስ ውጥን አላቸው፡፡
የሚመለከተው የመንግስት አካል እንዲደግፋቸውም በቦርድ ሰብሳቢያቸው በኩል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መንገደኞች የወጣቶቹን ጥረት ያደነቁ ሲሆን ማህበረሰቡ ከንክኪ ሊርቅና ንጽህናውን ሳይዘናጋ ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ባንተአይሞሉ ተግባሩ ጥሩ አመለካከትን በማህበረሰቡ ዘንድ ለመፍጠር እና ራስን ከቫይረሱ ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
“ይህ ሲሆን የተመለከትኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ያሉም ሲሆን “በቴሌቪዥንና በተለያዩ መንገዶች የተነገሩንን የእጅ አስተሳሰብ ዘዴዎች በተግባር ያየንበት ጥሩ ምሳሌ ነው” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
“ብዙውን ጊዜ ወደስራችን እንጂ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ልብ አንልም” ያሉት አሰለፈች ኃይሌ የተባሉ ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ህዝቡ ተባብሮ ታጥቦ ንጽህናውን ሊጠብቅ ቢችል የተሻለ እንደሚጠቀም ገልጸዋል፡፡
ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ ስለመሆኑ የገለጸልን ወጣት ዳኛቸው ፍቃዱ በበኩሉ የወጣቶቹ ተግባር በተምሳሌትነት የሚወሰድ ነው ብሏል፡፡
“እኛም በሰፈራችን ተግባሩን ለመጀመር ለሚመለከተው የአስተዳደር አካል ጥያቄ አቅርበናል”ም ነው ያለው፡፡
ንኪኪ በተለይ ሰላምታ አሁንም ድረስ አልቀነሰም የሚለው ወጣት ዳኛቸው “ምንም እንደማንሆን ባምንም እንኳን በመታጠብ ራሳችንን መጠበቅ አለብን” ሲል ያሳስባል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን 5 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል ያለው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአሁኑ ሰዓት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬ ጠቅለል ያለ መግለጫን የሰጠው ኢንስቲትዩቱ በለይቶ መቆያ ከነበሩ 113 ተጠርጣሪዎች 74ቱ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በላብራቶሪ ምርመራ በመረጋገጡ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉንና በለይቶ ማቆያ ሆነው የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን የሚጠባበቁ 34 ተጠርጣሪዎች እንዳሉ ገልጿል፡፡