የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት እና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ስለመሆኑም መከላከያው አስታውቋል
በግድቡ የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት እና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን-መከላከያ
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት እና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አስታወቋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አደም መሃመድ፣ የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ እና የሰራዊቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ግድቡን ጎብኝተዋል።
ሰራዊቱ የሀገሪቱን ሰላምና ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚያስችል የላቀ ብቃት ላይ ይገኛል ያሉት ጄኔራል አደም በግድቡ ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት እና አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ሰራዊቱ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሰራዊቱ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ህዝብና መንግስት የሰጡትን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ መሆኑን ያነሱት ጀኔራል አደም፥ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየወሩ ከደመወዙ በመቆጠብ የዜግነት ድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ጉብኝቱ ሰራዊቱ የግድቡ የግንባታ ሂደት ያለበትን ሁኔታ በመረዳት በአሁኑ ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ የሚነዙ አሉባልታዎችን ለመመከት ተነሳሽነት እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፥ የአየር ሃይሉን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡
በቀጠናው የሚቃጣን የትኛውንም የአየር ላይ ጥቃት ለመመከት ብሎም አስፈላጊውን አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነም ነው ተናገሩት፡፡
በጉብኝቱ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።
ከሚኒስቴሩ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እየተገነባ ያለውን የግድቡን የግንባታ ሂደት ተዘዋውረውም ተመልከተዋል።