ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መሰጠቱን እንደምትደግፍ ኬንያ አስታውቃለች
ኢትዮጵያና ኬንያ በግድቡ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት ድጋፍ አስፈላጊነት ላይ ተስማሙ
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ወደ ኬንያ አምርተው ከታላቁ ህዳሴ ግድብና ከሌሎችም የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መክረዋል፡፡
የግድቡን የድርድር ሂደቶች ለኬንያታ ያብራሩት ሣህለ ወርቅ ኢትዮጵያ ከሁሉም የናይል ተፋሰስ ሃገራት ጋር ለመስራት እና በሃገራቱ የተፈረሙ ስምምነቶች ብቻ መተግበራቸውን ለማረጋገጥ ያላትን ቁርጠኛነት አስረድተዋል፡፡
አፍሪካ የተፈጥሮ ሃብቶቿን በማልማት በዘላቂነት መጠቀም እንዳለባት የተናገሩት ኬንያታ ሃብቶቹን በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስቀምጠዋል፡፡
ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠቱ አስፈላጊነት ላይ የተስማሙት ፕሬዝዳንቶቹ ስለ አፍሪካ ህብረት ድጋፍ አስፈላጊነትም መክረዋል፡፡
መሪዎቹ የሃገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮችም ላይ ተወያይተዋል፡፡
ግንኙነቱን ከአሁን ቀደም በነበሩ የሁለትዮሽ የግንኙነት መንገዶች፣ከፍተኛ ኮሚሽኖች እና ጥምር የድንበር ኮሚሽነሮች/አስተዳደሮች በኩል ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ ስለመሆናቸውም ነው ያረጋገጡት፡፡
ኮሚሽኖቹ በእህትማማች ሃገራቱ መካከል ያለውን ምጣኔ ሃብታዊ፣ፖለቲካዊ እና የደህንነት ጉዳዮች ትብብር ለማሳደግ እና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ በመደበኛነት የሚገናኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹም አዘዋል፡፡
በቀጣናው ያጋጠመው የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በሃገራቱ ሊደቅን ስለሚችለው ምግብ ዋስትና ችግር አሳሳቢነትም መክረዋል፡፡ ለችግሩ አፋጣኝና ሁሉን አካታች ምላሽ ለመስጠት በሁለትዮሽና በቀጣናዊ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በኩልም በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አመራር ሰጪነትና በወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ዋና ጸሃፊነት ኢጋድን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ያደነቁት ፕሬዝዳንቶቹ ለቀጣናው የምጣኔ ሃብት እና ደህንነት ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት የሚችል ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን ቁርጠኛ ነንም ብለዋል፡፡
ኬንያን እንዲጎበኙ በፕሬዝዳንቱ ግብዣ የተደረገላቸው ሣህለ ወርቅ ግብዣውን ስለመቀበላቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡