በጥቃቱ 16 ሰዎች ሲጎዱ የ3 ሰዎች ህይወት አልፏል
በመንዝ መሃል ሜዳ ከተማ በደረሰ የቦምብ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት አለፈ
ትናንት እለተ ሰኞ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ/ም በመንዝ መሃል ሜዳ ከተማ በደረሰ የቦምብ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡
ጥቃቱ በከተማው በሚገኝ አንድ የመጠጥ ቤት ምሽት 1፡15 ላይ መፈጸሙን የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጥላሁን ደበበ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪው ቀደም ሲልም በባለቤቱ ላይ የመግደል ሙከራ ወንጀል ፈጽሞ ነበር፡፡ በሙከራው በባለቤቱ ወንድምም ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
በወንጀሉ በዋስ ቢለቀቅም ጉዳዩ በቀጠሮ የክስ ሂደት ላይ እንደነበር ነው ኢንስፔክተር ጥላሁን የተናገሩት፡፡
ከባለቤቱ ጋር የፍትሃብሄር ክርክር እንደነበረበትም ገልጸዋል፡፡
ይህን ምክንያት አድርጎ በቂም በቀል በመነሳሳት ጥቃቱን ሳይፈጽመው እንዳልቀረም ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ በባለቤቱ እናት (አማቱ) መጠጥ ቤት ላይ መብራት መጥፋቱን ተከትሎ ጨለማን ተገን በማድረግ የተፈጸመ ነው፡፡
በመጠጥ ቤቱ በር አሾልኮ በወረወረው ኤፍ ዋን ቦምብም በድምሩ በ16 ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 3 ሰዎችም ወዲያውኑ አንዳንዶቹም ደግሞ ወደ ህክምና ተቋም በመወሰድ ላይ ሳሉ ሞተዋል፡፡ የጥይት እና የስለት ጥቃትም አድርሷል፡፡
ቦምቡ ከተወረወረበት ክፍል ውጭ በሌላ ክፍል የነበሩትን አማቱን በሽጉጥ ተኩሶ የመታው ግለሰቡ ለህይወታቸው የሚያሰጋ ከፍተኛ ጉዳትንም አድርሶባቸዋል፡፡ ጥቃቱ ከተፈጸመበት ቤት ለመውጣት በመውጣት ራሳቸውን ለማዳን ሲሞክሩ በነበሩ ሁለት ሰዎችም ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ አንደኛውን በሽጉጥ ሌላኛውን ደግሞ በጩቤ ከወጋም በኋላ ነው የተሰወረው እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ገለጻ፡፡ በጩቤ የተወጋው 16 ዓመት ታዲጊ ነው፡፡
ቦምቡ በተወረወረበት ክፍል ውስጥ ከቤቱ ደንበኞች ጋር የነበረችው ባለቤቱ ግን አልተጎዳችም፡፡
የከተማው ኮሙኒኬሽን ተጨማሪ ብሎ በፌስቡክ ገጹ ከጉዳዩ ጋር መያያዝ አለመያያዙ ገና እየተጣራ ቢሆንም በተመሳሳይ ሰአት በተለምዶ ወልደመድክን ጫካ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ አስካሁን ማንነቱ ያልታወቀ አንድ ሌላ ሰው ጭንቅላቱ ላይ የስለት ጥቃት ደርሶበት ወድቆ መገኘቱንና ጉዳዩ እየተጠራ መሆኑን አስነብቧል፡፡ ይህም የሟቾቹን ቁጥር 4 ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡
ጥቃት ፈጻሚው ግለሰብ የመንግስት ሰራተኛ ነው፡፡ በፋይናንስ መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ በሂሳብ ኦዲተርነትም ይሰራል፡፡
ኢንስፔክተር ጥላሁን ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ ፖሊስ ፈጥኖ ደርሷል ብለዋል፡፡ ተጎጂዎች ህክምና እንዲያገኙ ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም ተጠርጣውን ለመያዝ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ግለሰቡም ወዲያውኑ ከስፍራው ተሰውሯል፡፡
ተጠርጣሪው ከአሁን ቀደም በፈጸመው ወንጀል ተሸሽጎ ከነበረበት በዘመዶቹ አግባቢነት ለፖሊስ እጅ መስጠቱን የተናገሩት ኃላፊው በቶሎ በቁጥጥር ስር በማዋል ከህግ ፊት ለማቅረብ ፖሊስ ክትትል ማድረግ መጀመሩንም ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡