114 ኪሎግራም ቀንሻለሁ ያለው ዩቲዩበር ትናንት እና ዛሬው ተከታዮቹን አስደምሟል
ኒኮላስ ፔሪ የተባለው አሜሪካዊ በሰባት ወር ውስጥ ያሳየውን “ተአምራዊ ለውጥ” በቪዲዮ አጋርቷል
አወዛጋቢው ዩቲዩበር “ትናንት ወፍራምና በሽተኛ ሲሉኝ የነበሩ ሰዎችን 114 ኪሎግራም በመቀነስ መሳሳታቸውን አሳይቻቸዋለሁ” ብሏል
ከምግብ ጋር የተያያዘ ይዘት ያላቸውን ቪዲዮዎች የሚያጋራው ዩቲዩበር ትናንት ባጋራው ምስል እንደ አዲስ ተገልጧል።
“ኒኮካዶ አቮካዶ” በሚል የዩቲዩብ ስም የሚታወቀው ኒኮላስ ፔሪ በሰባት ወራት ውስጥ 114 ኪሎግራም መቀነሱን ገልጿል።
ፔሪ ያጠለቀውን ጭምብል ሲያወልቅም እርሱ ነው ወይስ ሌላ ሰው በሚያስብል ደረጃ ተለውጦ ታይቷል።
“ሁለት እርምጃ ቀዳሚ” የሚል ርዕስ የሰጠው ቪዲዮ ከ23 ሚሊየን በላይ ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን፥ አድናቂዎቹ የግርምት አስተያየት እያጎረፉለት ነው።
በዩክሬን የተወለደው አሜሪካዊ ዩቲዩበር ባለፉት ሁለት አመታት አዲስ ቪዲዮ አለመስራቱን መግለጹም ሌላኛው መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር።
ፔሪ የሚለቃቸውን ቪዲዮዎች አስቀድሞ በመስራቱ ባለፉት ሰባት ወራት ያለምንም መዛነፍ በጊዜያቸው እየተጋሩ ሙሉ ትኩረቱን ክብደቱን መቀነስ ላይ ማድረጉን ተናግሯል።
ከእይታ በተሰወረባቸው ወቅቶች ራሱ በልብ ህመም ተጠቅቷል የሚሉና ሌሎች አሉባልታዎችን እያስነገረ ሲያደናግር መቆየቱንም ነው በለቀቀው ቪዲዮ ያመነው።
አወዛጋቢው ፔሪ የለቀቀው የ25 ደቂቃ ቪዲዮ በርካቶችን ከማስደንገጥ አልፎ ትችቶችንም እያስከተለ ነው።
ባለፈው አመት 40 ኪሎግራም ቀንሻለሁ ሲል መነጋገሪያ የነበረው ግለሰቡ ለአሁኑ ስኬቱ የተለየ አስተዋጽኦ የነበረውን ጉዳይ አላብራራም።
ይህም “ኒኮካዶ አቮካዶ” ምናልባትም በአጭር ጊዜ ክብደትን ለመቀነስ የሚውሉ መድሃኒቶችን ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል የሚሉ መላምቶች እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።
የባለፈውን አመት የክብደት ለውጡን ተከትሎ የሚሰራቸው ቪዲዮዎች በጤናማ አመጋገብ ላይ ብቻ ያተኮሩ እንዲሆኑ ያደረገው ፔሪ ግን ለተቺዎቹ ግድ እንደሌለው ገልጿል።
ከልክ ያለፈ ውፍረቱ ከማህበረሰቡ ያደርስበት የነበረው ተጽዕኖ ከባድ እንደነበር በማውሳትም “ትናንት ወፍራምና በሽተኛ ሲሉኝ የነበሩ ሰዎችን 114 ኪሎግራም በመቀነስ መሳሳታቸውን አሳይቻቸዋለሁ” ብሏል።
ኒኮላስ ፔሪ በዩቲዩብ ከ4 ሚሊየን በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን አነጋጋሪው ቪዲዮም የተከታዮቹን ቁጥር እንደሚያስመነድገው ይጠበቃል።