“እነ አቶ ልደቱ ወደ ሙሉ የፓርቲው የአባልነት ደረጃ ሳይሸጋገሩ በአመራርነት ሊቀመጡ ይችላሉ”- ኅብር ፓርቲ
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ የፊታችን እሁድ እንደሚሰበሰብ ፓርቲው ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቋል
ፖለቲከኞቹ ኅብርን “እንደ ግለሰብ” ነው ከአሁን ቀደም የነበረውን የፓርቲ መዋቅራቸውን ይዘው የሚቀላቀሉት
እነ አቶ ልደቱ እና ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር)ን ተቀላቅለዋል መባሉን ተከትሎ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበራ በቀለ ፖለቲከኞቹ “እንደ ግለሰብ” ፓርቲውን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ፖለቲከኞቹ “እንደ ግለሰብ” የሚቀላቀሉት ከአሁን ቀደም ህጋዊ ሰውነት ኖሯቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎቻቸው ምርጫ ቦርድ ያስቀመጠውን መስፈርት በወቅቱ አሟልተው አለማቅረባቸውን ተከትሎ በመሰረዛቸው ነው፡፡
አቶ ልደቱ በኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ብሄራዊ ምክር ቤት አባልነት፣ አቶ አዳነ ታደሰ በፓርቲው ሊቀመንበርነት፤ ኢንጂነር ይልቃል ደግሞ በኢትዮጵያ ሃገር ዐቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀመንበርነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡
የኢዴፓ እና የኢሃን ህልውና አቶ ልደቱ እና ኢንጂነር ይልቃል ከእስር እስከተለቀቁበት ጊዜ ድረስ ዘልቆ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ፓርቲዎቹ ከህብር ጋር በመሆን “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)” የተሰኘ ጥምረትን ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ፣ ምርጫው እንዲራዘም እና ብሄራዊ መግባባት እንዲመጣ እንዲሁም የሽግግር ጊዜ መንግስት እንዲመሰረት ሲጠይቁም ነበረ፡፡ ሆኖም የጋራ እንቅስቃሴያቸው በፖለቲከኞቹ እስር ምክንያት ተገቷል፤ ፓርቲዎቹም ተሰርዘዋል፡፡
ይህ በመሆኑም አሁን የአባላት ምልመላ ፎርምን ሞልተው ህብር ፓርቲን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡ ይህም ዛሬ በሚሰጡት የጋራ መግለጫ የሚፈጸም ይሆናል፡፡
ሲቀላቀሉ በዞን እና በወረዳ ያለ አደረጃጀታቸውን እንዲሁም አባሎቻቸውን ይዘው ነው የሚቀላቀሉት እንደ ምክትል ሊቀመንበሩ ገለጻ፡፡
ፖለቲከኞቹ ህብርን ሲቀላቀሉ እንደ ማንኛውም አዲስ አባል ወይስ በተለየ ሌላ ሚና እና ኃላፊነት ነው ሲል አል ዐይን የጠየቃቸው አቶ አበራ የፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ተቀባይነት ያላቸው አዳዲስ አባላት ወደ ሙሉ የፓርቲው የአባልነት ደረጃ ሳይሸጋገሩ በአመራርነት ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡
ይህም በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የጎላ ስም ያላቸው እነ ልደቱ አዲስ በሚቀላቀሉት ፓርቲ ውስጥ የመሪነት ሚና ኖሯቸው ሊንቀሳቀሱ በመጪውም ምርጫ ሊሳተፉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡
ሆኖም ይህ በየደረጃው ባሉ የፓርቲው የአመራር አካላት የሚወሰን ነው፡፡
የማዕከላዊ ኮሚቴውን ምናልባትም የጠቅላላ ጉባዔውንም ውሳኔ ይሻል እንደ አቶ አበራ ገለጻ፡፡ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚም የፊታችን እሁድ ይሰበሰባል፡፡
“ኅብር ራሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ነው”ያሉት አቶ አበራ ከአሁን ቀደም አደረጃጀት ኖሯቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፓርቲ አመራሮች ፓርቲውን መቀላቀላቸው በመጪው ምርጫ የጎላ እንቅስቃሴን ለማድረግ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡
“ከአሁን ቀደም በአብሮነት ስንንቀሳቀስ በነበርንበት ወቅት ሲሰነዘሩብን የነበሩ ጫናዎችን ለመቋቋም አቅም ይፈጥርልናል” ሲሉም ነው ምክትል ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡
ኅብር የ5 ፓርቲዎች ማለትም ቱሳ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ፣ የኦሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት እና ደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ውህድ ነው፡፡
በመጪው ሃገር አቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን መስፈርት አሟልተው የምርጫ ቦርድን እውቅና ካገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከልም ይገኛል፡፡
በምርጫው የመወዳደሪያ አርማው “አዲስ እና ብሩህ ተስፋን የሚያመለክተው አደይ አበባ” እንዲሆንለት ለቦርዱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን ፓርቲው ለአል ዐይን አስታውቋል፡፡