ዛግ ፡ ሃገር በቀሉ የመተንፈሻ ቬንትሌተር
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባደረገው የውድድር ጥሪ 323 ዓይነት ፕሮጀክቶች በ446 ተመዝጋቢዎች ቀርበዋል
በሐዋሳ በሶስት ጓደኛሞች ተሰርቷል
ዛግ የተሰኘ የመተንፈሻ ቬንትሌተር በሐዋሳ ተሰራ
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የCOVID-19 ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎችንና ሃሳቦችን እያወዳደረ በሚገኝበት innovation.covid19.et ከደረሱ ፈጠራዎች መካከል አንዱ ዛግ የተሰኘ የመተንፈሻ ቬንትሌተር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቬንትሌተሩ ንድፍ በሀገር ውስጥ የተዘጋጀ ነው ያለው ጽህፈት ቤቱ በሐዋሳ ከተማ በሚኖሩ ሦስት ጓደኛሞች፣ በአካባቢው ከሚገኙ ግብአቶች መሰራቱን ገልጿል።
የሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና ባለሞያዎችም በምርት ሂደቱ በማማከር ተሳትፎ አላቸው።
ጽህፈት ቤቱ የማኅበረሰብን ፍላጎት በመረዳት ፈጠራ የታከለበት ምላሽ በመስጠት፣ ዜጎች ለሀገር ልማት አዎንታዊ ሚናን ይጫወታሉ ያለም ሲሆን ለተሻለ ማኅበረሰብ ግብአት የሚሆኑ ሐሳቦችን በማፍለቅ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የማኅበራዊ ድጋፍን በማሳለጥ፣ የአካባቢ ጥበቃን በማላቅ እና በሌሎችም ፈጠራዎች የተሳትፎ ጥሪው ለሁላችንም ቀርቧል ብሏል።
በውድድሩ “ተገቢ፣በአጭር ጊዜ ሊተገበሩ የሚችሉ ሐሳቦች፣ ናሙናዎች፣ ምርትና አገልግሎቶች ናቸው” የተባሉ 323 ዓይነት ፕሮጀክቶች በ446 ተመዝጋቢዎች ለመወዳደሪያ ቀርበዋል።
ከ323ቱ 80ዎቹ ለሁለተኛ ዙር ሲያልፉ 30ዎቹ ለመጨረሻ ዙር የውሳኔ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ስለመቅረባቸው ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በውድድሩ የተሳተፉ የፈጣራ ሃሳብ ባለቤቶችን ከሰሞኑ ማመስገናቸው የሚታወስ ነው፡፡