ለጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውም ሰነድ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የለውም
“ግብጽ የትም ብትሄድ ኢትዮጵያ ማልማቷን አታቆምም”-አምሳሉ ትዕዛዙ ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ
ግብጽ የሶስቱን ሀገራት የውይይትና የድርድር ሃሳብ በመተው ወደሌሎች ሀገሮችና ተቋማት መሄዷ ኢትዮጵያን ከልማቷ እንደማያስተጓጉላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ተጠባባቂ ቃል አቀባይ አምሳሉ ትዕዛዙ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ግብጽ የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ ከሰሞኑ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰነድ ብታቀርብም በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሦስቱ ሀገራት በሚያደርጉት ውይይት እንጅ ወደ ሌሎች ሀገራት ወይም ተቋማት በመሄድ አሊያም ሰነድ በመላክ እንደማታምንም አቶ አምሳሉ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግብጽ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ልካዋለች የተባለው ሰነድን በተመለከተ በቀጣይ ምላሽ እንደሚሰጥም ተጠባባቂ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ግብጽ የህዳሴ ግድብ በየዓመቱ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሄም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል ስጋት አላት፡፡ ከግድቡ የዉሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በሶስቱ ሀገራት መካከል የመጨረሻ ስምምነት ሳይደረስ የዉሀ ሙሌት እንዳይጀመር የሚል መግለጫ፣ ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ግምጃ ቤት መውጣቱ ይታወቃል፡፡ ግብጽ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ አቤቱታ ከሰሞኑ ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርባለች፡፡