እግዳው በዛንዚባር በሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን እንደማይመለከት ተገልጿል
ዛንዚባር ጸጉራቸውን ሽሩባ በሚሰሩ ወንዶች ላይ እገዳ ጣለች።
በታንዛኒያ ስር ያለችው ራስ ገዟ ዛንዚባር ወንዶች ጸጉራቸውን እንዳይጎነጉኑ ወይም ሽሩባ እንዳይሰሩ ከልክላለች።
የዛንዚባር ባህል፣ፊልም እና ኪነ ጥበብ ሀላፊ ዶክተር ኦስማን አዳም እንዳሉት እገዳ የተጣለው የረስገዝ አስተዳድር የሆነችው ዛንዚባር ባህልን ለመጠበቅ በማለም ነው ብለዋል።
ጸጉራቸውን ተሰርተው በተገኙ ሰዎች ላይም ፖሊስ እርምጃ ይወስዳል የተባለ ሲሆን ድርጊቱን ፈጽሞ የተገኘ የሀገሪቱ ዜጋ አንድ ሚሊዮን ሽልንግ አልያም 409 ዶላር ቅጣት እንደሚከፍል ተገልጿል።
ዛንዚባር ወንዶች ጸጉራቸውን አሳድገው እንደሴቶች እንዳይሰሩ የሚከለክለውን ህግ በፈረንጆቹ 2015 ላይ ያወጣች ቢሆንም ሳይተገበር ቆይቷል ተብላል።
ይሁንና ይህ አነጋጋሪ ህግ በዛንዚባር ያሉ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ወይም ለጉብኝት የመጡ የሌላ ሀገር ዜጎችን እንደማይመለከት ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ዛንዚባር ይህን ህግ ተግባራዊ ማድረጋን ተከትሎ ተቃዋሚዎች እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ህጉ የዜጎችን መብት የሚጋፋ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ሌሎች ደግሞ ህጉ የዛንዚባርን ባህል ለመጠበቅ እና ከመጤ ባህሎች የሚጠብቅ ነው ሲሉ የመንግሥትን ውሳኔ ደግፈው አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው።