3 ሚሊየን ዶላር የሚያሸልመውን “የዛይድ ሰስቴነቢሊቲ ሽልማት” እነማን ወሰዱ?
በ2008 የተጀመረውን ሽልማት ለመውሰድ ከ152 ሀገራት 4 ሺህ 538 ተወዳዳሪዎች ተፎካክረዋል
በዛሬው እለትም በአምስት ዘርፎች አሸናፊ የሆኑት ይፋ የተደረዱ ሲሆን፥ 3 ሚሊየን ዶላሩ ይከፋፈላሉ
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሼክ ዛይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ስም የሰየመችው ሽልማት ዘንድሮም የአየር ንብረት ላይ አዲስ የመፍትሄ ሃሳብ ይዘው የመጡ አካላት ተሸልመውበታል።
“የዛይድ ሰስቴነብሊቲ ሽልማት” በጤና፣ በምግብ፣ በአየር ንብረት፣ በውሃ እና በአለም አቀፍ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ፣ ዘመናዊ እና ዘላቂ እድገትን የሚያበረታቱ ስራዎችን የከወኑ እጩ ተፎካካሪዎችን የሚሸለሙበት ነው።
በፈረንጆቹ 2008 የተጀመረው “የዛይድ ሰስቴነብሊቲ ሽልማት” እስካሁን በ150 ሀገራት በሚኖሩ 370 ሚሊየን ሰዎች ህይወት ላይ አዎንታዊ ሚና የነበራቸው ሰዎች እንደተሸለሙበትም ነው የተገለጸው።
በዚህ አመትም 3 ሚሊየን ዶላር ሽልማቱን ለመውሰድ ከ152 ሀገራት 4 ሺህ 538 ተወዳዳሪዎች ማመልከቻ አስገብተዋል።
በርካታ አመልካቾችን በማስመዝገብ ኬንያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ግብጽ፣ ብራዚል እና አሜሪካ ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል።
በዛሬው እለትም በአምስቱም ዘርፎች አሸናፊ የሆኑት ተለይተው የተሸለሙ ሲሆን፥ አሸናፊ የሆኑት የተመደበውን 3 ሚሊየን ዶላር ይከፋፈላሉ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የንግድ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሱልጣን አል ጀበር (ዶ/ር) ሽልማቱ ሲበረከት ባደረጉት ንግግር፥
ሽልማቱ ባለፉት 15 አመታት አካታች እድገትን እና የህዝብን ችግር በመሰረታዊነት የሚፈቱ ፕሮጀክቶችን የሚያፈልቁ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ማፍራቱን ተናግረዋል።
በሽልማቱ 3 ሚሊየን ዶላሩን የሚከፋፈሉ ተሸላሚዎች በየዘርፉ፦
በጤና ዘርፍ - የብራዚሉ ኤክስፔንዲሽነሪ ሶሳይቲ ፎር ሄልዝ
ድርጅቱ ተንቀሳቃሽ ቀዶ ህክምናን የሚያደርግ፣ ዘመናዊ የህክምና ቁሳቁሶች እና የኤሌክትሪክ ጀነሬተር ያለው ሲሆን፥ በአማዞን በኩል 35 ሺህ ሰዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተጋ ያለ ተቋም ነው።
በምግብ ዘርፍ - የፈረንሳዩ “ኢንሴክት” ፕሮጀክት
ፕሮጀክቱ ለ30 ሚሊየን ሰዎች የተመጣጠነ ምግብን ማስገኘት የሚያስችሉ ግብአቶችን ያቀርባል፤ በአሳ ልማት ላይ ለተሰማሩ ወገኖችም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ሌሎች ግብአቶችን እያቀረበ የሰዎች የምግብ ስርአት ጤናማ እንዲሆን በመስራት ላይ ይገኛል።
በኢነርጂ ዘርፍ - የዮርዳኖስ “ኒዩሮቴክ” ፕሮጀክት
ፕሮጀክቱ በዮርዳኖስ ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ሶሪያውያን ስደተኞች አስተማማኝና ከብክለት የጸዳ የሃይል አማራጭን ይዞ የመጣ ነው።
በውሃ ዘርፍ - ባንግላዲሽ
የባንግላዲሽ የውሃ አመራሮች በሀገሪቱ ያለውን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለመቀነስ የተከተሉት የሃብት አጠቃቀም ዘዴ በአቡ ዳቢ አሸልሟቸዋል። በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ 15 ሺህ 881 አባዋራዎች ለመስኖ እና ለመጠጥ የሚሆን ውሃ በዘላቂነት የሚያገኙበትን ሞዴል መፍጠራቸው ለሽልማት እንዳበቃቸውም ተገልጿል።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዘርፍ - የፊጂ፣ የባንግላዲሽ፣ የጀርመን፣ የኮሎምቢያ፣ የኢራቅ እና ታንዛኒያ ተቋማት
የፊጂው ከመል ሙስሊም ኢንስቲትዩት” ኢንስቲትዩቱ በአመት 219 ሜጋዋት የኤሌትሪክ ሃይል የሚያመነጭ ፕሮጀክትን ወደ ስራ በማስገባት ለ6 ሺህ 150 ተመሪዎች ምግብ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
በባንግላዲሽ የሚገኘው “ዳካ ሞዴል ሪዚደንሺያል ኮሌጅም ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የሀገሪቱ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር፣ ኬሚካሎች እና የአፈር ማከሚያዎችን በማከፋፈል ምርታማነትን በማሳደግ ተሸላሚ ሆኗል።
የጀርመኑ የሮናልድ ጂምናዚየም ትምህርት ቤትም የኤሌክትሪክ ሃይል ከጸሃይ ሃይል ለማመንጨት በተማሪዎቹ ባቀረበው አሳማኝ ፕሮጀክት ለሽልማት በቅቷል፤ ፕሮጀክቱ የትምህርት ቤቱን የታዳሽ ሃይል ጥገኝነት በ10 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል።
የኢራቁ “ስኩል ፎር ዘ ጊፍትድ” እና በታንዛኒያ የዩናይትድ ወርልድ ኮሌጅ አሩሻ ካምፓስ በተማሪዎቻቸው በቀረቡ የህብረተሰቡን ችግር በሚያቀሉ ፕሮጀክቶች የ”ዛይድ ሰስቴነቢሊቲ ሽልማት” አሸናፊ ሆነዋል።
የኮሎምቢያው ፒዩስ ቴራ ትምህርት ቤትም የ200 ሺህ ነዋሪዎችን ለአየር ብክለት ተጋላጭነት የሚቆጣጠር ስርአትን በማስተዋወቅ ሽልማቱን ወስዷል።