ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ በጂዳ ከሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ ጋር ተወያዩ
አሜሪካ እና ዩክሬን የሶስት አመቱን ጦርነት ለማስቆም እና በቅርቡ የሻከረውን ግንኙነታቸውን ለማደስ ከዛሬ ጀምሮ በሳኡዲ ይመክራሉ

የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በዚህ ሳምንት የማዕድናት ስምምነቱን እንደሚፈርሙ ይጠበቃል ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ከሳኡዲ አረቢያ ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጋር ተወያዩ።
በጂዳ በተካሄደው ምክክር ልኡል አልጋወራሹ ሪያድ የዩክሬኑ ጦርነት እንዲቆም እና የሰላም ስምምነት እንዲደረስ በአለማቀፍ ደረጃ የተጀመሩ ጥረቶችን ትደግፋለች ማለታቸውን የሳኡዲ ብሄራዊ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ሳኡዲ የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ የማሸማገል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
ሞስኮ እና ኬቭ በርካታ የጦር ምርኮኞችን እንዲለዋወጡ ከማስማማት ባለፈ በጦርነቱ ምክንያት ግንኙነታቸው የተካረረው አሜሪካ እና ሩሲያ ባለፈው ወር ንግግር እንዲጀምሩ ማድረጓ ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ አቻቸው ጋር ሊገናኙ የሚችሉት በሪያድ መሆኑን መናገራቸውም አይዘነጋም።
በዛሬው እለት ደግሞ የአሜሪካ እና ዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመክሩበትን መድረክ አዘጋጅታለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ባለፈው ወር በነጩ ቤተመንግስት ከትራምፕ ጋር ንትርክ ውስጥ ገብተው ያለስምምነት ከወጡ በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ በጊዜያዊነት አቋርጣለች። ከሳተላይት ምስሎች የሚገኙ መረጃዎችንም ለኬቭ እንደማታጋራ ገልጻለች።
በሳኡዲው የአሜሪካ እና ዩክሬን ምክክር ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ አይሳተፉም፤ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትሮቻቸውን ጨምሮ አራት ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውን ልከዋል። አሜሪካም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማርኮ ሩቢዮ እና ሌሎች አመራሮች ትወከላለች።
የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጫና የበረታባቸው ዜለንስኪ በቅርብ ቀናት ውስጥ ወደ ዋይትሃውስ ተመልሰው የማዕድን ስምምነቱን ሊፈርሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ በሶስት አመት ውስጥ ለዩክሬን ያደረገችውን ከ350 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ኬቭ በማዕድን ሃብቷ ልትመልስል ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
ከዋሽንግተን ጋር ግንኙነቷን ለማደስ ንግግር የጀመረችው ሞስኮ በኬቭ ላይ የተጠናከረ የሚሳኤልና ድሮን ጥቃት መፈጸሟን የቀጠለች ሲሆን፥ ተጨማሪ መንደሮችን መቆጣጠሯንም አስታውቃለች።
ባለፈው ሳምንት ብቻ 870 የድሮን እና ከ80 በላይ የሚሳኤል ጥቃት አድርሳለች የሚኡት ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ስምምነቱ የብስን ብቻ ሳይሆን አየር እና ባህርን ሊያካትት ይገባል ብለዋል።
ክሬምሊን ግን በፈረንሳይ እና ብሪታንያ የቀረበውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ለኬቭ ጊዜ መግዣ ነው በሚል ተቃውሞታል።