ጣሊያን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለዩክሬን ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ እና ሌሎች ድጋፎችን አድርጋለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ በጣሊያን ጉብኝት እያደረጉ ነው።
ፕሬዝዳንቱ ሮም እንደገቡ ባሰፈሩት የትዊተር መልዕክት፥ “ዩክሬን ለድል በተቃረበችበት ወቅት የሚደረግ ወሳኝ ጉብኝት” እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዜለንስኪ በቆይታቸው ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እና ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ጋር ይመክራሉ ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ወደ ቫቲካን በማምራትም ከሮማ ካቶሎካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ጋር እንደሚወያዩም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
አባ ፍራንሲስ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚደረግ ንግግር አሸማጋይ ሆነው ለመቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ቫቲካን 15ኛ ወሩን የያዘው ጦርነት የሚቋጭበትን የሰላም ስምምነት ረቂቅ እያዘጋጀች ስለመሆኑ ባለፈው ወር መናገራቸውንም የቢቢሲ ዘገባ አውስቷል።
ይሁን እንጂ ሞስኮም ሆነች ኬቭ ስለቫቲካን የሰላም እቅድ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ መግለጻቸው አይዘነጋም።
አባ ፍራንሲስ የዩክሬን ጦርነት እንደተጀመረ ምዕራባውያኑ በሩሲያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች መቃወማቸውና “ኔቶ በሩሲያ በር ላይ እየጮኸ ነው” የሚል አስተያየታቸውን ለጣሊያን ጋዜጣ መስጠታቸው ኬቭና አጋሮቿን ማስቆጣቱ ይታወሳል።
ሊቀ ጳጳሱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ፕሬዝዳንት ፑቲንን ፊት ለፊት ለማነጋገር ፍላጎት እንዳላቸውና በዩክሬን ምድር ላይ የሚፈጸመው ውድመት እንዲቆም በመወትወት በምዕራባውያኑ የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ማለዘባቸው ነው የሚነገረው።
ለዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ባስተላለፉት ጥሪም ለሰላማዊ ንግግር ዝግጁ እንዲሆኑ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ዛሬ በቫቲካን ከአባ ፍራንሲስ ጋር በሚያደርጉት ውይይትም ቫቲካን አዘጋጅቸዋለው ስላለችው የሰላም እቅድ ዙሪያ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በዛሬው እለት ከጀርመን የ3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል የተገባላት ዩክሬን፥ ከጣሊያን ሊደረግላት ስለሚችለው ድጋፍ ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩም ነው የተገለጸው።
ጣሊያን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለዩክሬን ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወታደራዊ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረጓን መረጃዎች ያሳያሉ።