የዩክሬን "የድል እቅድ" በአጋሮች ፈጣን ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ዘለንስኪ ተናገሩ
ዘለንስኪ በዚሁ ጉዳይ ከባይደን ጋር ንግግር ለማድረግ በቀጣይ ሳምንት ወደ አማሪካ ያቀናሉ
ዘለንስኪ ለድል እቅዱ ስኬት በተለይ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሚና በጣም አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል
የዩክሬን "የድል እቅድ" በአጋሮች ፈጣን ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ነው ሲሉ ዘለንስኪ ተናገሩ።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ያላት "የድል እቅድ" ስኬት ሁሉም አጋሮች በሚወስዱት ፈጣን ውሳኔ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንኪ ትናንት ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ዩክሬንን እየጎበኙ ካሉት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ቮን ደር ሊየን ጋር ሆነው በሰጡት መግለጫ ዩክሬን ለአየር ጥቃት መከላከያ፣ ለኃይል እና ለሀገር ውስጥ መሳሪያ ግዥ ከህብረቱ ብዙ ቢሊዮን ዶላር ተበድራ የመጠቀም እቅድ አቅርባለች።
ዘለንስኪ ለድል እቅዱ ስኬት በተለይ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ሚና በጣም አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል። ዘለንስኪ በዚሁ ጉዳይ ንግግር ለማድረግ በቀጣይ ሳምንት ወደ አማሪካ ያቀናሉ።
"በእቅዱ የተካተቱ አብዛኞቹ ውሳኔዎች በባይደን ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ሌሎች አጋሮችም አስፈላጊ ናቸው፤ ነገርግን የአሜሪካን መልካም ፈቃድ እና ድጋፍ የሚፈልጉ የተወሰኑ ነጥቦች አሉ" ብለዋል ዘለንስኪ።
ዘለንስኪ ስለእቅድ ዝግጁቱ ያለውን ሁኔታ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ የእቅዱ ይዘት ምን እንደሆነ አላብራሩም።
"አጠቃላይ እቅዱ አጋሮቻችን በሚያሳልፉት ፈጣን ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ነው። አጋሮቻችን ውሳኔ ካሳለፉ በኋላ ከጥቅምት -ታህሳስ ባለው ጊዜ ውስጥ ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል ዘለንስኪ።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ሰላም ማምጣት ብቻ ሳይሆን ሀገራቸውን ለሚያጠናክረው ለዚህ እቅድ ባይደን ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ተማምነዋል።
"ዩክሬን በእሳቸው(ባይደን) ድጋፍ ላይ ትተማመናለች" ብለዋል ዘለንስኪ።
ጦርነቱ ዩክሬን ነጻነቷን ለማረጋገጥ እና አለምአቀፍ ህግን ለማስከበር የሚደረግ በመሆኑ "ዩክሬን ስታሸንፍ መላው አለም ያሸንፋል ያሉት ዘለንስኪ የአሜሪካ ድጋፍ ፍትሃዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዩክሬን ሩሲያ የሚያደርጉት ጦርነት 31 ወራትን አስቆጥሯል።
ዩክሬን በምስራቅ ዩክሬን የተሰማራውን የሩሲየ ኃይል ለማዛባት ባለፈው ነሐሴ ወር በምዕራብ ሩሲያ ክርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት ከፍታ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ችላ ነበር።
ነገርግን የሩሲያ ኃይሎች ማጥቃታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ወሳኝ የተባለችውን ፖክሮቭስክ ከተማ ለመያዝ ተቃርበዋል።
ዩክሬን ምዕራባውያን ሀገራት የለገሷትን የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት ብትጠይቅም እስካሁን አልፈቀዱላትም።
ፑቲን ምዕራባውያን ለዩክሬን ፍቃድ የሚሰጧት ከሆነ ቀጥተኛ ጦርነት ይቀሰቀሳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ።