ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የዘመናችን ምርጥ የሽያጭ ባለሙያ መሆናቸውን ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በሄደበት ሀገር ባዶ እጁን አይመለስም ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል
የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት መቆም አለበት የሚሉት ትራምፕ ዩክሬን ከአሜሪካ የወሰደችውን ልትከፍለን ይገባል ብለዋል
ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የዘመናችን ምርጥ የሽያጭ ባለሙያ ናቸው ሲሉ ተናገሩ፡፡
አሜሪካን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ዋነኛ የቅስቀሳ አጀንዳቸው ሆኗል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በኦሂዮ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በታሪክ ምርጡ የሽያጭ ሰው ናቸው፡፡ ወደ ሀገራችን በመጡ ቁጥር 50 እና 60 ቢሊዮን ዶላሮችን ይዘው ይመለሳሉ” ብለዋል፡፡
“ዩክሬን ከአሜሪካ የወሰደችውን ገንዘብ ልትከፍለን ይገባል” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ እኔ ብሆን ይህን አላደርገውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲ ዋነኛ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የፊታችን ህዳር ወር ላይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን የአሜሪካዊያንን ገንዘብ ለዩክሬን እየሰጠ እና ዓለምን ወደ ሶተኛው ጦርነት እየገፋት ነው የሚሉት ትራምፕ ምርጫውን ካሸነፉ በ24 ሰዓት ውስጥ ጦርነቱን አስቆመዋለሁ ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ አባል ሀገራት ዓመታዊ መዋጫቸውን ካላዋጡ ከሩሲያ ጥቃት ቢደርስባቸው አሜሪካ ድጋፍ እንደማታደርግ መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡
የትራምፕን ንግግር ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ወደ ጦር ግምባር እንደሚጓዙ እና እውነታውን እንዲረዱ እንደሚያደርጉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ወደ ጦር ግምባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝዳንትነት ሊመረጡ ይችላሉ በሚል በማሰብ ላይ ሲሆን አውሮፓ ራሷን መከላከል የምትችልበትን አቋም መገንባት አለባት የሚሉ ሀሳቦች በአባል ሀገራቱ እየተነሳ ይገኛል፡፡
የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳድር ለዶናልድ ትራምፕ ንግግሮች በሰጠው ምላሽ የምረጡኝ ቅስቀሳን እንደ እውነት እና ፖሊሲ አትዩት ብሏል፡፡