ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የባለፈው ሳምንት የኋይት ሀውስ ፍጥጫ “አሳዛኝ” ነው ሲሉ ተናገሩ
ዘለንስኪ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ግንኙነታቸውን ማሻሻል እንደሚፈልጉ እና ጦርነቱ በሚቆምበት ሂደት ዙሪያ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕ እና ዘለንስኪ ድጋሚ እንዲገናኙ ለማድረግ ጥረት ላይ ናቸው
የባለፈው ሳምንት የኦቫል ኦፊስ ፍጥጫን “የሚያሳዝን” ሲሉ የገለጹት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ዘለንስኪ ይህን ያሉት ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ እርዳታ ማቋረጣቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ነው፡፡
"ዩክሬን ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በተቻለ ፍጥነት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመምጣት ዝግጁ ነች። ከዩክሬናውያን የበለጠ ሰላም የሚፈልግ የለም ፤ እኔና ቡድኔ ዘላቂ ሰላም ለማግኘት በፕሬዝዳንት ትራምፕ ጠንካራ አመራር ስር ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል ።
ባሳለፍነው ሳምንት በኋይት ሀውስ ኦቫል ኦፊስ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራፕ እና ከምክትላቸው ጋር የተደረገውን ዱላ ቀረሽ ውይት አስመልክቶ ዘለንስኪ በሰጡት አስተያት “እንደዛ መሆኑ በጣም ያሳዝና፤ ነገሮችን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው። የወደፊቱ ትብብር እና ግንኙነት ገንቢ እንዲሆን እንፈልጋለን ለዚህም ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል"፡፡
ወታደራዊ ድጋፍ መቋረጡን ተከትሎ ዩክሬን ከአሜሪካ ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ እንዳልደረሳት የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ከዋሽንግተን ማረጋገጫ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
"የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር፣ የስለላ ኤጀንሲዎቻችን ኃላፊዎች እና ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር እንዲያነጋግሩ እና ይፋዊ መረጃ እንዲያገኙ አዝዣለሁ” ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር ደግሞ “አሜሪካ እና ዩክሬን በመከባበር ላይ የተመሰረተ ንግግር ማድረግ ይኖርባቸዋል በተለይም በዚህ ጦርነት ወቅት የሰዎችን ህይወት ከሞት ከመጠበቅ አኳያ ተመሳሳይ አቋም ሊያንጸባርቁ ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ዘለንስኪ በተጨማሪም ዩክሬን ከዋሽንግተን ጋር በልዩ ማዕድናት እና በደህንነት ዙሪያ ጠቃሚ የሆነ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል ።
ትራምፕ ማክሰኞ መገባደጃ ላይ ለኮንግረሱ ባደረጉት ንግግር ከዘለንስኪ ደብዳቤ እንደደረሳቸው እና አሜሪካ ዩክሬን ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን እንድትጠብቅ ምን ያህል ድጋፍ እንዳደረገች ኪየቭ እውቅና መስጠቷን አስታውቀዋል።
ዘለንስኪ ለአሜሪካ እውቅና እና ምስጋና የሚቸር ደብዳቤ መላካቸውን እንደሚያመሰጉኑ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተመሳሳይ “ከሩስያ ጋር ጠንካራ ውይይት አድርገናል ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን የሚያሳዩ ጠንካራ ምልክቶችንም አግኝተናል” ብለዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የአውሮፓ መሪዎች ትራምፕ እና ዘለንስኪ ድጋሚ እንዲገናኙ ለማድረግ ጥረት ላይ ናቸው፡፡
ከፕሬዝዳንቱ ጋር የስልክ ውይይት ያደረጉት ማክሮን የሀገራቱ ተቀራርቦ መነጋገር ጦርነቱን በአፋጣኝ ለማስቆም ያለውን ሚና መግለጻቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል፡፡