አሜሪካ ለወሳኝ ማዕድናት ያቀረበችው እቅድ ኢፍትሃዊ ነው- የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ
ዩክሬን ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የዩክሬንን ወሳኝ ማዕድናት እንድታገኝ የሚያስችል የተሻሻለ ረቂቅ ስምምነት ለዋሽንግተን ልካለች

ዘለንስኪ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ፕሬዝደንት ፑቲን ድጋሚ ጦርነት እንዳይጀምሩ አሜሪካ ለዩክሬን የቃል ሳይሆን ተጨማሪ የሆነ የደህንነት ዋስትና ልትሰጣት ይገባል ብለዋል
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስካ አሜሪካ ለወሳኝ ማዕድናት ያቀረበችው እቅድ ኢፍትሃዊ ነው አሉ።
ዘለንስኪ አሜሪካ ወሳኝ የዩክሬይን ማዕድናትን ለማውጣት ያቀረበችው ሀሳብ ፍትሃዊ አይደለም፤ እቅዱ የዩክሬንን የደህንነት ዋስትና አላከታተም ሲሉ ተናግረዋል።
ዩክሬን ባለፈው ሳምንት አሜሪካ የዩክሬንን ወሳኝ ማዕድናት እንድታገኝ የሚያስችል የተሻሻለ ረቂቅ ስምምነት ለዋሽንግተን ልካለች።
"ይህ ሰነድ አላለቀም፤ እዚህ ላይ አንፈርምም ብያቸዋለሁ። በዚህ ሰነድ ላይ መስራታችንን እንቀጥላለን" ሲሉ በቱርክ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ዘለንስኪ መናገራቸውን ሮይተርስ የቱርኩን አናዶሉን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዘለንስኪ "በሀገራችንና በሀብታችን ላይ ለምታደርጉት ኢንቨስትመንት ክፍት ነን... ነገርግን የሆነ ነገር የምንሰጣችሁ ከሆነ የሆነ ነገር መቀበል አለብን" ብለዋል።
"ለየትኛውም አህጉር የጥሬ እቃ ማዕከል መሆን አንፈልግም።"
ብርቅ ወይም ውድ ማዕድናት እንዲሁም ቲታኒየም፣ዩራኒየምና ሊቲየም አሜሪካ ከምትፈልጋቸው ማዕድናት ውስጥ ይገኙበታል። ዋሽንግተን ለዩክሬን ስታደርገው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማስቀጠል ቁርጠኛ ያልሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ዋሽንግተን ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍ እንድትቀጥል 500 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ብርቅ ማዕደናትን እንደሚፈልጉ እየተናገሩ ነው።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በአንካራ ያደረጉት ጉብኝት የአሜሪካና የሩሲያ ባለስልጣናት ያለዩክሬን ተሳትፎ በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ በሳኡዲ አረቢያ ካደረጉት ስብሰባ ጋር ተገጣጥሟል።
ዘለንስኪ ዩክሬን የዋሽንግተን ድጋፍ አላት ብለው ቢያምኑም ከትራምፕ የበለጠ ድጋፍ ይፈልጋሉ።
"ፑቲንን ከፖለቲካ መገለል(አሜሪካ )ማውጣቷን አይተናል፤ ያ የእነሱ ውሳኔ ነው። ነገርግን 'ጦርነቱን ለማስቆም ይሄ የእኛ እቅድ ነው' ስትል ጥያቄ ያስነሳል። የት ነን? በድርድሩ ጠረንጴዛ ላይ ነን። ይህ ጦርነት እየተካሄ ያለው ዩክሬን ውስጥ ነው" ብለዋል ዘለንስኪ።
ዘለንስኪ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ፕሬዝደንት ፑቲን ድጋሚ ጦርነት እንዳይጀምሩ አሜሪካ ለዩክሬን የቃል ሳይሆን ተጨማሪ የሆነ የደህንነት ዋስትና ልትሰጣት ይገባል ብለዋል።