አሜሪካ እና ሩስያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ተስማሙ
በ2022 የዩክሬን ጦርነት መጀመርን ተከትሎ ሀገራቱ ይፋዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠው ቆይተዋል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ይህ ወር ከመጠናቀቁ በፊት ከፑቲን ጋር ሊገናኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል
ሩሲያ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደ መደበኛ ግንኙነት ለመመለስ ተስማምተዋል፡፡
በሳኡዲ አረቢያ ሪያድ ውይይት ላይ የሚገኙት የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባላስልጣናት የተቋረጠውን ግንኙነት ለማስቀጠል ተስማምተዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በቀድሞው የአሜሪካ አስተዳደር በሞስኮ ላይ ተጥለው የነበሩ የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ እቀባዎች መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በቅርቡ ሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናቶችን ለመሾም እና ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደሚጀምሩ ነው የገለጾት፡፡
የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በዋሽንግተን እና ሞስኮ የሚገኙ የሀገራቱ ኢምባሲዎች የዲፕሎማቶችን እና የኢምባሲ ሰራተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል፡፡
ማርኮ ሩብዮ ሁለቱ ሀገራት በዩክሬን ጦርነት፣ በሁለትዮሽ እና በሌሎች ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በተቀላጠፈ መንገድ በጋራ ለመስራት በአፋጣኝ የድፕሎማሲ ሁኔታቸውን ያሻሽላሉ ነው ያሉት፡፡
ባለፈው ወር ስልጣን የያዙት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ድርድር እንዲጀምሩ ካዘዙ በኋላ የሪያዱ ንግግር ጦርነቱን ለማስቆም አንድ እርምጃ ነው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚያደርጉት የፊት ለፊት ግንኙነት ይህ ወር ከመጠናቀቁ በፊት ሊካሄድ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከሳኡዲው የልኡካን ቡድን ውይይት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዩክሬን በስብሰባው አልተሳተፍኩም ወቀሳን አጣጥለዋል፡፡
“ዛሬ ላይ በሰላም ድርድሩ ላይ አልተሳተፍኩም የምትለው ኪቭ የዛሬ ሶስስት አመት በፊት የት ነበረች፣ ከአመታት በፊት ጦርነቱን ተደራድሮ የማስቆም ሰፊ እድል ነበራት” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጦርነቱን የያዙበትን መንገድ ያጣጣሉት ትራምፕ ዩክሬን በቅርቡ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዋን ማድረግ እንደሚኖርባት አሳስበዋል፡፡
ትራምፕ አክለውም አውሮፓውያን ከሰሞኑ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ የሰላም አስከባሪ ኃይል በዩክሬን ለማሰማራት ያቀረቡትን ሀሳብ እንደማይቃወሙ ተናግረዋል፡፡