የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ አሜሪካ አመሩ
ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር በዋሸንግተን ይወያያሉ ተብሏል

አሜሪካ እና ዩክሬን የማዕድን ልማት ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ አሜሪካ አመሩ፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት ሩሲያ ለጥቂት ቀናት በሚል ልዩ ዘመቻ ጦሯን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባሳለፍነው ሕዳር ወር ላይ በተካሄደው ምርጫ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋል ጦርነቱ የሚቆምበት መላ እየተፈለገ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ ለዩክሬን ዋነኛ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ አድራጊ የነበረችው አሜሪካ ድጋፏን አቁማለች፡፡
ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን ለሰጠችው በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች መልሽልን አልያም ማዕድንሽን ስጪኝ የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥያቄ ውድቅ አድርገናል ቢሉም የማዕድን ስምምነቱን ለመፈራረም በዛሬው ዕለት ወደ ዋሸንግተን አምርተዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ወደ ዋሸንግተን ከማምራታቸው በፊት በአየርላንድ መዲና ደብሊን አምርተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ሚካኤል ማርቲን ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡
ዩክሬን አሁን ላይ እና ወደፊት ተፈላጊ የሚሆኑ ውድ ማዕድናት መገኛ ስትሆን በተለይም ብረት፣ ዩራኒየም፣የከሰል ድንጋይ፣ሊቲየም እና ሌሎች ተፈላጊ ማዕድናት አሏት፡፡
እንደ ፎርብስ ዘገባ ከሆነ ዩክሬን 15 ትርሊዮን ዶላር የሚያወጣ ማዕድናት ያሏት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 350 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ብረት እና ሊቲየም ማዕድናት የሚገኙት ሩሲያ በተቆጣጠሯቸው ግዛቶች ውስጥ ነው፡፡
ዩክሬን ማዕድናቷን ለአሜሪካ ለመስጠጥ በጫና ተስማታለች የተባለ ሲሆን ስምምነቱን ለመፈጸም ግን ከሩሲያ ለሚደርስባት ጥቃት የደህንነት ዋስትና ከአሜሪካ ትፈልጋለች ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው አሁንም ከዩክሬን ጋር ስምምነት እንዳልተደረሰ እና ውይይቶች በመካሄድ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡