ዚምባቡዌ ፖሊሶች ለስራ ሲሰማሩ ሞባይል ስልካቸውን እንዳይጠቀሙ አገደች
በመዲናዋ ሃራሬ ሁለት ትራፊኮች ከአሽከርካሪዎች ጉቦ ሲቀበሉ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች በተዘዋወረ ማግስት ነው ውሳኔው የተላለፈው
የዚምባቡዌ ፖሊስ በሀገሪቱ በሙስናና ብልሹ አሰራር ከተበላሹ ተቋማት መካከል እንደሚመደብ ይነገራል
የዚምባቡዌ መንግስት ፖሊሶች ለስራ ሲሰማሩ ሞባይል ስልካ እንዳይዙና እንዳይጠቀሙ አገደ።
ሁሉም ፖሊሶች ለስራ ሲሰማሩ ስልካቸውን ለበላይ ሃላፊዎቻቸው አስረክበው መውጣት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
ለፖሊሶች ተልኳል የተባለው የማሳሰቢያ መልዕክት መንስኤ እና አለማው ግን አልተጠቀሰም።
ከእረፍት ስአት ውጪ ፖሊሶች ሞባይል ስልካቸውን መጠቀም እንዳይችሉ የተላለፈው ውሳኔ ሙስናን ለመቀነስ ያለም ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሁለት የትራፊክ ፖሊሶች ከሰሞኑ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻዎችን እና ሞተሮችን እያስቆሙ ከአሽከርካሪዎች ጉቦ ሲቀበሉ የሚያሳይ ምስል ተለቋል።
ቪዲዮው ወትሮውንም በሙስና የተዘፈቁ ናቸው የሚባልላቸውን የሀገሪቱን የትራፊክ ፖሊሶች ገመና የገለጠ ነው በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የዚምባቡዌ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፖል ንያቲ ሁለቱ ጉቦ ሲቀበሉ የታዩ የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላአውን ተናግረዋል።
“ለፖሊስ አገልግሎት የማይመጥኑ” ሲሉ የገለጿቸውን ባልደረቦቻቸው አስተዳደራዊ ቅጣትና የወንጀል ክስ እንደሚጠብቃቸውም ነው ያነሱት።
ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዚምባቡዌ ተቋማት በሙስና ቢፈተኑም የትራፊክ ፖሊሶች ያፈጠጠ ጉቦ የመጠየቅ ልምድ ግን አሳሳቢ ስለመሆኑ ዜጎች ያነሳሉ።
ሀራሬ ባለፈው ወርም ይህንኑ ችግር ይቀንሳል ያለችውን ውሳኔ አሳልፋ ነበር፤ ፖሊሶች ለስራ ከጣቢያ ሲወጡ ስልካቸውን እንዳይዙ የሚከለክል መመሪያ አውጥታ ተፈጻሚ ግን አልሆነም።
“ምንም እንኳን ተደጋጋሚ ማሳሳቢያ ብናሰማም ትዕዛዙን የበላይ አዛዦች ሊያስፈጽሙት አልቻሉም” የሚለው አዲሱ የእገዳ ደብዳቤ፥ ፖሊሶች ከምሳ ስአት እና ከእረፍት ውጪ ስልካቸውን በስራ ስአት መጠቀም እንደማይችሉ አመላክቷል።
የተላለፈውን ውሳኔ የማያስፈጽሙ የፖሊስ አመራሮች ስልካቸውን ይዘው ለስራ ወጥተው በተገኙት ፖሊሶች ምትክ ለግዳጅ እንዲሰማሩ ይደረጋሉም ነው የተባለው።