በኮሮና ቫይረስ ወቅት ብዙ ትርፍ ቀንቶት የነበረው ዙም ኩባንያ መክሰሩን ገለጸ
ኪሳራውን ተከትሎም 15 በመቶ ሰራተኞቹን እና ደመወዝ ቅነሳ መጀመሩን አስታወቋል
የዙም ኩባንያ ዓመታዊ ትርፍ ከ340 ሚሊዮን ዶላር ወደ 48 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል
በኮሮና ቫይረስ ወቅት ብዙ ትርፍ ቀንቶት የነበረው ዙም ኩባንያ መክሰሩን ገለጸ፡፡
የቪዲዮ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ተመራጭ የሆነው ዙም መተግበሪያ በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሁነኛ የስራ ማስኬጃ ሆኖ ነበር፡፡
ይሄንን ተከትሎ ይህ የአሜሪካ መተግበሪያ ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ ከፍተኛ ትርፍ ካስመዘገቡ የዓለማችን ኩባንያዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
አሁን ላይ የዓለም እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ቦታዎቹ በመመለስ ላይ በመሆኑ ምክንያት የዙም መተግበሪያ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየቀነሰ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡
በዚህም ምክንያት ዙም ኩባንያ 15 በመቶ ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ የገለጸ ሲሆን በስራቸው በሚቀጥሉ ሰራተኞች ላይም የደመወዝ ቅነሳ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ኤሪክ ዩዋን ዙም ኪሳራ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ በፈረንጆቹ 2020 ላይ 340 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ያገኘው ዙም አሁን ላይ ትርፉ ወደ 48 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱን አብራርተዋል፡፡
ዙም ኩባንያ በ2022 ላይ ላስመዘገበው ኪሳራ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እና ገዳይነት ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ሰዎች በቤት ሆነው ሲሰሩ ለተፈጠረው ፍላጎት ምላሽ እንዲሰጡ የተቀጠሩ ሰራተኞች ደመወዝ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ዩዋን ጠቅሰዋል፡፡
ዙም መተግበሪያ በፈረንጆቹ 2011 ላይ የተመሰረተ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ መከሰት ትልቅ የገበያ እድል እና መታወቅን አትርፎለታል፡፡