በአፋር ክልል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ድጋፍ እንደሚፈልጉ ክልሉ ገለጸ
በአፋር ክልሉ 450ሺ ዜጎች መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግስት ገልጿል
በጦርነቱ ምክንያት በአፋር ክልል የ10 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ንብረት መውደሙን መነሻ ጥናት እንደሚያሳይ ክልሉ ገልጿል
በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ክልሎች አንዱ በሆነው አፋር ክልል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ድጋፍ እንደሚፈልጉ ተገለጸ፡፡
የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ በጦርነቱ ምክንያት1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት እርዳት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህ ዜጎች ውስጥ ደግሞ 450 ሺ የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
- በጦርነት ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው የነበሩ 728 ህጻናትን ማገናኘቱን ተመድ ገለፀ
- ህወሓት ይዟቸው በነበረው በአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች ከ480 በላይ ንጹሃንን ገድሏል- ፍትህ ሚኒስቴር
በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎች በ14 የመጠለያ ጣቢዎች እንደሚገኙ ያነሱት አቶ መሐመድ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ድጋፍ እየተገኘ ቢሆንም ገና ያልተሰጡ እንዳሉም አንስተዋል፡፡
በኮሚሽኑ በኩል መዘግየቶች እንዳሉ የገለጹት ኃላፊው የተጠየቀው ድጋፍ በሙሉ ያለመምጣት ችግርም እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ላይ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በዓለም ምግብ ፕሮግራም እየተረዳ እንደሆም ኃላፊው ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱና እንደተጎዱ የጸጥታ አካላት ጥናት እያደረጉ መሆኑን የገለጹት አቶ መሐመድ ጥናቱ ሲጠናቀቅ በሚመለከታቸው አካላት ይፋ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚሰራም ክልሉ አስታውቋል፡፡
በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት የ10 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ንብረት መውደሙን የተደረገው መነሻ ጥናት እንደሚያመለክት የተናገሩት አቶ መሐመድ ሁሴን ቀጣይ ጥናትም እየተደረገ እንደሆነም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳ በመነሻ ጥናቱ በክልሉ የ10 ቢሊዮን ብር የንብረት ውድመት መድረሱ ቢገለጽም የአጥኝዎች ቡድን ተዋቅሮ ዝርዝር ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ጦርነቱ በአራት ዞኖች 21 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የተጠቀሰ ሲሆን በነዚህ ቦታዎች የነበሩ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ስለወደሙ አገልግሎት መስጠት አልተጀመረም ተብሏል፡፡
በጥናቱም ጦርነቱ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ፣ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ ፣ስነልቦናዊ ጉዳቶች ምን ያህል እንደሆኑ እንደሚያሳይም ኃላፊው አንስተዋል፡፡ የአፋር ሕዝብ በሕወሃት ጥቃት እየተሰነዘረበትም ጭምር ሰብዓዊ ድጋፍ ወደ አፋር እንዲያልፍ በማድረግ ከጦርነትም በላይ በሰብዓዊነት ላይ ትልቅ ድል እንደተገኘም ነው የተገለጸው፡፡
ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁሉንም ሕዝብ በእኩል አይን እንዲመለከቱ ጥሪ ያቀረቡት ኃላፊው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከአፋር ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከ8 ወራት በኋላ መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታሳል፡፡
ነገርግን ህወሃት የፌደራል መንግሰትን የተናጠል ተኩስ አቁም እንደማይቀበለው በመግለጽ በአፋር እና አማራ ክልሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር በርካታ ቦታዎች ተቆጣጥሮ ነበር፡፡
ህወሃት በአማራ ክልል ስድስት ዞኖች ላይ ወረራ መፈጸሙን የክልሉ መንግስት የገለጸ ሲሆን በአፋር ክልል ደግሞ በአራት ዞኖች 21 ወረዳዎች ላይ ወረራ መፈጸሙን የአፋር ክልል አስታውቋል፡፡
የፌደራል መንግስት የህወሃትን ጥቃት ለመመከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅና የመንግስት አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ ወደ ግንባር እንዲዘምቱ ከወሰነ በኋላ ህወሓትን ከምስራቅ አማራና ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ ማስቀጣቱ ገልጿል፡፡
ህወሃት በአንጻሩ “ለሰላም እድል ለመስጠት” ሲባል ከሁለቱ ክልሎች መውጣቱን ይገልጻል፡፡