“እንደ ፓርቲ ከህወሃት ጋር መነጋገር አንፈልግም”- የአፋር ሕዝብ ፓርቲ
ህወሃት በአፋር ክልል ሰሜናዊ አቅጣጫ አዲስ ጥቃት መክፈቱንም ፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም ገልጸዋል
የአፋር ሕዝብ በህወሃት በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱንም አቶ ሙሳ ገልጸዋል
ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ንግግር እና ድርድር ማድረግ እንደማይፈልግ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ አስታወቀ።
የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም፤ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሁን ላይ በሕዝብ ላይ ትንኮሳ እንዲሁም ጥቃት እያደረሰ ካለው የህወሃት ቡድን ጋር እንደ ፓርቲ መነጋገርም መሆነ መደራደር እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል።
አቶ ሙሳ ፤ ህወሃት ትናንትና ከሰዓት በኋላ በሰሜን አፋር በኩል አዲስ ጥቃት መክፈቱንም ተናግረዋል። በመጀመሪያ በአፋር ክልል በራህሌ ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበር አቶ ሙሳ አስታውሰዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ፤ ህወሃት የአብአላ ከተማን ለመቆጣጠር ሶስት እና አራት ጊዜ ሙከራ ማድረጉን ገልጸው በአካባቢው ያለው የአፋር ሕዝባዊ ሰራዊት ይህንን ጥቃት እየመከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ከስር መሰረቱ የተቋቋመው ህወሃት በሕዝብ ላይ ሲፈጽመው የነበረውን የረጅም ዘመናት ግፍና መከራን ለመታገል እንደሆነ ያነሱት አቶ ሙሳ ፓርቲያቸው ፤ ከሕወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኑነትም፣ ንግግርም፣ ድርድርም እንደማይፈልግ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቀዋል።
አቶ ሙሳ፤ እንደ ፓርቲ ከህወሃት ጋር ድሮም ምንም ንግግር እንዳልነበር የገለጹ ሲሆን፤ ወደፊትም ንግግር ሊኖር እንደማይችልም ገልጸዋል።
“ህወሃት የአፋርን ሕዝብ ብዙ መከራ አብልቷል” ያሉት ሊቀ መንበሩ የፓርቲውን አመራሮች አሸባሪ ብሎ ፈርጆ እንደነበር ገልጸዋል።
እንደ ፓርቲ ግን ከህወሃት ጋር መነጋገር እንደማይፈልግ የገለጹት አቶ ሙሳ፤ እንደ ሀገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተነጋግሮ ችግሮቹን በጠረንጴዛ ዙሪያ መፍታት ከቻለ “እኛም እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም የምናገኝበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወስነውን አብረን የምንወስን ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።
“በፓርቲያችን በኩል ግን ከነሱ ( ከህወሃት) ጋር ምንም አይነት ነገር ሊኖረን አይችልም የሚል ቁርጠኛ አቋም ይዘናል” ሲሉም አቶ ሙሳ ተናግረዋል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ እንደ ግንቦት ሰባት እና ኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ሁኑ ነፍጥ አንስቶ በኤርትራ በረሃ ትግል ሲያደርግ የነበረ ፓርቲ መሆኑ ይታወሳል።
አፋር ክልል ተሰሚነት ካላቸው ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሀገሪቱ ርዕሰ መስተዳድር ከሆኑ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ገብቷል።
ፓርቲው እ.ኤአ. 2010 ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ መሳተፉ ይታወሳል።
አፋር ሕዝብ ፓርቲ በ 2013 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምንት ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 96 ዕጩዎችን አቅርቦ ነበር።