10 በስደተኞች ተመራጭ የሆኑ ሀገራት
የጎግል የፍለጋ ውጤቶች መሰረት ያደረገ ጥናት ከመላው አለም ሰዎች ሊሰደዱባቸው የሚመርጧቸውን ሀገራት ዝርዝር ይፋ አድርጓል
ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ የበርካቶች ምርጫ ሆነዋል ተብሏል
የሰሜን አሜሪካዋ ሀገር ካናዳ ከመላው አለም ሰዎች ሊኖሩባት የሚመርጧት ሀገር ሆናለች።
“ፈርስት ሙቭ ኢንተርናሽናል” የተሰኘ ተቋም የጎግል የፍለጋ ውጤቶችን መሰረት ያደረገ ጥናት አድርጎ በርካቶች ለስደት የሚመርጧቸው 10 ሀገራትን ይፋ አድርጓል።
ባለፈው አመት ከ1.5 ሚሊየን በላይ “እንዴት ወደ ካናዳ መሄድ እችላለሁ” የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ጎግል ላይ መቅረባቸውን ነው ጥናቱ ያሳየው።
በዚህም ካናዳ በርካቶች አዲሷ ቤታቸው ሊያደርጓት የሚመኟት ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች የሚለው ኒወርክ ፖስት፥ ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ከውብ ተፈጥሮዋና ምቹነቷ ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ሀገሬውን ማማረር መጀመሩን ይጠቁማል።
አውስትራሊያ ደግሞ ካናዳን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን፥ ወደ ሀገሪቱ ለመግባት በሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ጥያቂዎች ጎግል ላይ ቀርበዋል ብሏል “ፈርስት ሙቭ ኢንተርናሽናል”።
የደሴቶች ምድሯ ኒውዝላንድ የአውሮፓዎቹን ስፔን እና ብሪታንያ ስታስከትል፥ ፖርቹጋልና ጃፓን ደግሞ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ከአመታት በፊት የበርካቶች ምርጫ የነበረችው አሜሪካ ግን እስከ 10ኛ ባለው ዝርዝር ውስጥ አልገባችም።