ፑቲን ዶላር “የሚታመን መገበያያ” እንልዳሆነ ገልፀዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሀገራቸው ከዚህ በኋላ ጋዝ የምትሸጠው በራሷ የመገበያያ ገንዘብ “ሩብል” እንዲሆን መወሰናቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ ወደ አውሮፓ የሚደረገው የጋዝ ሽያጭ በሩሲያ ገንዘብ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፈዋል ነው የተባለው። የዚህ ውሳኔ ተግባራዊነትም በፍጥነት እንደሚከናወን ሞስኮ አስታውቃለች።
ሩሲያ ቱዴይ (አርቲ) የተባለው መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው ሞስኮ ከዚህ በኋላ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ጋር “በዩሮም ሆነ በዶላር የመገበያየት ስሜት የላትም” ብሏል።
ቭላድሚር ፑቲን ዶላር የሚታመን የመገበያያ ገንዘብ እንዳልሆነ መናገራቸውን ሩሲያ ቱዴይ (አርቲ) ዘግቧል።
የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ እና የካቢኔ አባላት ከአውሮፓ ጋር በሩብል የሚካሄደውን ግብይት በተመለከተ በአንድ ሳምንት ውስጥ ውሳኔ እንዲያስቀምጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምንም እንኳን የተለያዩ ሀገራት የሩሲያን ሀብት ቢያግዱም ሀገራቸው ግን በገባችው ውል መሰረት ነዳጅ ማቅረቧን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ክምችት መቀነሱንና ፍላጎት ደግሞ በአራት ሚሊዮን በርሜል መጨመሩን ገልጸዋል።
በካስፒያን ባህር ባለው ነዳጅ ማስተላለፊ በኩል ነዳጅ ባለመግባቱ ጭማሪ ታይቷል ተብሏል።
አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ አሁን ላይ በ 118 ነጥብ 61 ዶላር እየተሸጠ ነው።
የሩሲያን ምርቶች ለአውሮፓና ለአሜሪካ የሚሸጡት በራሷ በሩሲያ መገበያያ ገንዘብ እንዲሆን የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ሕብረት የተሰጠ አስተያየት እስካሁን አልተደመጠም።