ዩክሬን መተላለፊያውን የዘጋችው አካባቢውን የተቆጣጠሩት የሩሲያ ወታደሮች ጣልቃ እየገቡ ነው በሚል ነው
ዩክሬን የሩሲያ ጋዝ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የሚተላለፍበትን ቁልፍ መስመር (ፓይፕ) ዘጋች፡፡
ኪቭ የሶክራኒቭካ መተላለፊያን የዘጋችው አካባቢውን የተቆጣጠሩት የሩሲያ ወታደሮች ቴክኒካል በሆኑ ነዳጅ የማስተላለፍ ስራዎች ጣልቃ እየገቡ ነው በሚል ነው፡፡
ከዛሬ ረቡዕ ጀምሮ በሶክራኒቭካ በኩል ጋዝ ወደ አውሮፓ ማስተላለፉን እንደሚያቆምም የሃገሪቱ የጋዝ መተላፊያዎች አስተዳደር (GTSOU) አስታውቋል፡፡
እርምጃው በአውሮፓ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ንረት የበለጠ እንዳያባብሰው ተሰግቷል፡፡
ሩሲያ ወደ አውሮፓ ከምታስተላልፈው ነዳጅ ሶስት እጅ ያህሉ በሶክራኒቭካ የሚተላለፍ ነው፡፡
ዩክሬንም መተላለፊያ መስመር ሆና በማገልገሏ ትጠቀማለች፡፡ በወጉ አስተላልፋ ለተጠቃሚ የአውሮፓ ሃገራት ማድረስም አለባት፡፡
ዋናውን ማስተላለፊያ በመዝጋቷ በራሷ የሚደርስባት ጉዳት እንደሌለ የገለጸችው ዩክሬን ለአውሮፓ ሃገራት አቅጣጫውን በመቀየር በሌላ የማስተላለፊያ መስመር ነዳጅ እንደምታደርስ አስታውቃለች፡፡
ሆኖም የነዳጅ ኤክስፖርት ጉዳይ የሚመለከተው ዋናው የሩሲያ የነዳጅ ኩባንያ ጋዝፕሮም የመተላፊያ መስመሩን ቀይሮ ጋዝ ማስተላለፉ ቀላል አይደለም ብሏል፡፡