የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ “ከ100 በላይ የጭነት መኪኖች” መቀሌ ደረሱ
በትግራይ “ከ90% በላይ የሚሆኑ ዜጎች” አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ኦቻ ገልጿል
በትግራይ ያለው ሁኔታ ተባብሶ “ረሃብ” እንዳያጋጥም በርካታ የዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋታቸው ሲገልጹ ቆይተዋል
የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ከ100 በላይ የጭነት መኪኖች ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ደርሰዋል፡፡
3500 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና ህይወት አድን የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ከ100 በላይ የጭነት መኪኖች መቀሌ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ቢሮ አስታውቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎትን ለመሸፈን የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና አጋር የረድኤት ድርጅቶች አስፈላጊውን አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉም ቢሮው አስታውቋል።
- በትግራይ ክልል ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ወደ ውይይት መምጣት አለባቸው- የፀጥታው ም/ቤት
- ተመድ የትግራይን ጉዳይ በአጀንዳነት ያንሳው እንጂ የሚፈታው በኢትዮጵያ አመራር ነው-ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
በትግራይ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ለረሃብ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ጽ/ቤት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ገልጾ ነበር፡፡
አሁን በትግራይ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመግታት 203 ሚልዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የዓለም ምግብ ፕሮገራም ጠቁሟል፡፡
የዓለም ምግብ ፕሮገራም ቃል አቀባይ ቶምሰን ፊሪ"5.2 ሚልዮን የትግራይ ህዝብ ( 91% የሚሆነው ህዝብ) አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል" ሲሉ ከቀናት በፊት ከጀኔቫ ተናግረው ነበር፡፡
"ለምግብ እጥረት ስለተጋለጡት እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው በርካታ ሰዎች እጅጉን ተጨንቀናል" ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
በትግራይ ያለው ሁኔታ እጅጉን አሳሰቢ በመሆኑ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት መፍትሄ እንዲሻ ከፍተኛ የተመድ ባለስልጣኑ ማርክ ሎውኮክ ማስጠንቀቀቻውም ይታወሳል፡፡
የተመድ ከፍተኛ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪው ማርክ ሎውኮክ " የእርዳታ ስርጭቱን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ማሳደግና ማዳረስ ካልተቻለ በትግራይ ረሃብ የመከሰቱ እድል ከፍተኛ ነው" ማለታቸውን ኤኤፍፒ ከአራት ቀናት በፊት ዘግቦ ነበር፡፡
በትግራይ ላለው ችግር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሃት መካከል ጥቅምት ወር 2013ዓ.ም የተጀመረው ግጭት 11 ወራትን አስቆጥሯል።
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሃት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ ሙሉ ትግራይ መቆጣጠር ቻሉ።
የህወሃት ሃይሎች ከትግራይ አልፈው በአማራና አፋር ክልል ጥቃት በመክፈት የተወሰኑ ቦታዎችን መቆጣጠራቸው ይታወቃል። አሁን ላይ ጦርነቱ እየካሄደ ያለው በአማራ አፋር ክልል ውስጥ ሆኗል።
የፌደራል መንግስትም የተናጠል ተኩስ አቁም የተፈለገውን ለውጥ አላመጠም በማለት መከላከያና የክልል ልዩ ሃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ ትእዛዝ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ህወሃት በወረራቸው አካባቢዎች ግድያና መጠነ ሰፊ ዘረፋ ፈጽሟል በማለት ይከሳል።
በመንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሃት ግን በሁለቱ ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን አምኖ፤ በንጹሃን ላይ ጥቃት አድርሷል የሚለውን ክስ እያስተባበለ ይገኛል።