የዘንድሮው የዐድዋ ድል በዓል በመላ ሃገሪቱ ነው የሚከበረው ተባለ
ለማክበር የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ነው የተነገረው
የድል በዓሉ ለ126ኛ ጊዜ “ዐድዋን ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል በመላ ሃገሪቱ እንደሚከበር ተገልጿል
የዘንድሮው የዐድዋ ድል በዓል በመላ ሃገሪቱ ነው የሚከበረው ተባለ፡፡
በዓሉን በመላ ሃገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተነግሯል፡፡
የዘንድሮው የድል በዓል “ዐድዋን ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበርም ነው የተገለጸው፡፡
በዓሉን በፌዴራል ደረጃ በድምቀት ለማክበር ባለቤት ሆነን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራን ነው ያሉት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ የአከባበር ስነ ስርዓቱ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
በዓሉን በደመቀ ሁኔታ በመላ ሃገሪቱ ለማክበር የሰላም ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማኅበር፣የቅርስ ባለሥልጣን፣መከላከያ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት የተካተቱበት ዐቢይ ኮሚቴ፣ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን ምሁራንን፣ ዲፕሎማቶችን እና ዲያስፖራውን የሚያሳትፍ ዐውደ ጥናት (ሲምፖዚየም) እንደሚኖርም ተናግረዋል፤ ዐውደ ርዕዮች እና ስፖርታዊ ሁነቶች የስነ ስርዓቱ አካል ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ።
በዓሉ በክልል ደረጃ በተመሳሳይ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ጠቁመዋል። አዲስ አበባ መስተዳድር እና ኦሮሚያ ክልል በጋራ በአዲስ አበባ እንዲያከብሩት እየተሰራ እንደሆነም ነው አቶ ቀጀላ የተናገሩት፡፡
ዐድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ትልቅ በታሪክ የተመዘገበ ድል ነው ያሉት ሚኒስትሩ ወጣቱ ከዐድዋ ድል ሃገር ወዳድነትን እና ለአገር ነጻነት መቆምን መማር አለበት ብለዋል።
ሁሉም ሕዝብ በነቂስ በመውጣት በዓሉን እንዲያከብርና ለበዓሉ የተዘጋጀውን ኤግዚቢሽን እንዲጎበኝም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያን በአጼ ሚኒሊክ እየተመሩ ቅኝ ሊገዛ የመጣውን የፋሽት ወራሪ ኃይል በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ድል አድርገው በመላው ጥቁር ህዝብ ድልነት የሚጠቀስ አዲስ ታሪክ መጻፋቸው የሚታወቅ ነው፡፡