በድርጅቱ የታዛቢነት መቀመጫ ያላት ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ነው
13ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ በአረብ ኢምሬትሷ አዱ ዳቢ መካሄድ ተጀመረ።
በአቡ ዳቢ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ያለው የሚኒስትሮች ጉባዔው ''በንግድ ለሕዝብ መድረስ'' በሚል መሪ ቃል ካዘሬ ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ቀጥሎ ይካሄዳል።
በጉባኤው ላይ 175 የድርጅቱ አባላት፣ የታዛቢነት ደረጃ ያላቸው አባላት፣ የግሉ ዘርፍ መሪዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በድርጅቱ የታዛቢነት መቀመጫ ያላት ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ እየተሳተፈች ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትርና የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪ ገብረመስቀል ጫላ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሁሴን ኢትዮጵያን ወክለው በጉባኤው ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
13ኛው የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት በባለብዙ ወገን የንግድ ስምምነቶች ላይ መግባባት ለመፍጠር ይነጋገራሉ።
ዛሬ በአቡዳቢ በተጀመረው ኤግዚቢሽን ማዕከል በተጀመረው 13ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ የኮሞሮስና ቲሞር የአባልነት ጥያቄ አጽድቋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን በድርድር አባል ለመሆን በታዛቢነት መሳተፍ የጀመረችው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2003 ነው።