ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ተመለሱ
ዩክሬን በየዕለቱ 200 ወታደሮቿን እያጣች መሆኑን ገልጻች
ከ106 ቀናት በፊት በተጀመረው በዚህ ጦርነት 7 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል
ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ስደተኞች ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ተገለጸ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመሩ 106ኛ ቀናቸውን ይዘዋል፡፡
በዚህ ጦርነት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ተሰደው የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ድንበር ኤጀንሲ እንዳሳወቀው ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ስደተኛ ዩክሬናውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገልጿል፡፡
ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ፖላንድ እና ሮማኒያ የተሰደዱ ዩክሬናዊያን ወደ ሀገራቸው በተመድ ድጋፍ በመመለስ ላይ ሲሆኑ መኖሪያ ቤታቸው የወደመባቸው ዜጎች ወደተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እየገቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ 200 የዩክሬን ወታደሮች በየዕለቱ እየሞቱ መሆኑን የፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ረዳት ገልጸዋል፡፡
የዩክሬን ወታደሮች ከሩሲያ ጦር ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት በየዕለቱ 200 ወታደሮች እየተገደሉ መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ልዩ ረዳት ሚካሎ ፖዶሊያክ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ ጦር የዶምባስ እና ሉሃንስክ ግዛቶችን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ውጊያ የዩክሬን ወታደሮች በምዕራባዊያን እርዳታ ውጊያቸውን ቀጥለዋል ተብሏል፡፡
የሑለቱ ሀገራት ጦርነት በተቀረው ዓለም ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ሲሆን በተለይም የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ስጋት የገባው የአፍሪካ ህብረትም ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ዙሪያ ያጠመደችውን ፈንጂ እንድታጸዳ ጠይቋል፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ሩሲያን ጎብኝተው በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ይገኛሉ፡፡
ማኪ ሳል በሞስኮ ቆይታቸው ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ስንዴ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ሩሲያ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል እንደገቡላቸው ተናግረው ነበር፡፡