ሩሲያ፤ ዩክሬን በጥቁር ባህር የጭነት መርከቦች መተላለፊያ የቀበረችውን ፈንጅ እንድታጸዳ ጠየቀች
ሩሲያ ስንዴ ጭነው በቦስፎረስ ሰርጥ በኩል ለሚተላለፉ መርከቦች ከቱርክ ጋር በመተባበር ከለላ እንደምትሰጥ አስታውቃለች
ሞስኮ ዓለም ለገጠመው የእህል ኤክስፖርት ቀውስ ዩክሬንን ተጠያቂ አድርጋለች
ሩሲያ ዓለም ለገጠመው የእህል ኤክስፖርት ቀውስ ዩክሬንን ተጠያቂ አደረገች፡፡
ሞስኮው የግብርና ምርቶች ኤክስፖርት መስተጓጉሉ በዩክሬን ምክንያት የመጣ ነው በሚል ለዓለም እንደ ዓለም ላጋጠመው የምግብ እጥረትና የዋጋ ንረት ኪቭን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩ ሶግሉ በአንካራ መክረዋል፡፡
ምክክሩ በዋናነት በዓለም የምግብ አቅርቦት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ችግሩ በዋናነት ዩክሬን በጥቁር ባህር በቀበረችው ፈንጅ ምክንያት ያጋጠመ እንደሆነ የገለጹት ላቭሮቭ ባህሩን እንድታጸዳ ጠይቀዋል፡፡
ላቭሮቭ ሩሲያ እህልን በማያዣነት እንደማትጠቀም በመግለጽ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሃገራቸው ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱም አሳስበዋል፡፡
ሆኖም ዩክሬን "ባዶ" ስትል የላቭሮቭን ንግግር አጣጥላለች፡፡
ሩሲያ ምግብን እንደ “ድብቅ ሚሳዔል” እየተጠቀመችበት ነው- አውሮፓ ህብረት
ሩሲያ ዓለም ለምግብ እጦት እንዲዳረግ አሲራለች መባሉን የተቃወሙት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የጭነት መርከቦች ከዩክሬን ወደቦች የሚጭኑበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሃገራቸው ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ፕሬዝዳንት ፑቲን ጭምር ዋስትና መስጠታቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
ሃገራቸው ስንዴ ጭነው በቦስፎረስ ሰርጥ በኩል ለሚተላለፉ መርከቦች ከቱርክ ጋር በመተባበር ከለላ እንደምትሰጥም ላቭሮቭ ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ዓለም ለከፋ የምግብ እጦት እየተዳረገ ነው ያለው የዓለም የምግብ ድርጅት ከአሁን ቀደም ለፕሬዝዳንት ፑቲን ተማጽኖ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡
ከሰሞኑ ወደ ሞስኮ ያቀኑት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በአፍሪካ የስንዴ እና የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጉዳይ ላይ ከፑቲን ጋር መነጋገራቸውም ይታወሳል፡፡
ሩሲያ የምንጊዜም የአፍሪካ አጋር መሆኗን የገለጹት ፑቲን የስንዴ እና የሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡