ሚኒስትሮቹ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያም ይነጋገራሉ ተብሏል
የሩሲያ እና ቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሩሲያና ዩክሬን መካከል የሰላም ንግግሩ እንዲመለስ ለመጀመር ያለመ ውይይት መጀመራቸው ተገለጸ፡፡
ሰርጌ ላቭሮቭ ከቱርኩ አቻቸው ሜቭሉት ካቩሶግሉ ጋር ውይይት መጀመራቸውን የሩሲያ እና የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሚኒስትር ላቭሮቭ ወደ ቱርክ እንደሚያቀኑ በገለጸው መሰረት ዛሬ ሚኒስትሩ አንካራ ገብተዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር እንደሚያደርጉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል፡፡ መስሪያ ቤቱ፤ የሩሲያ እና ቱርክ መሪዎች ዘጠኝ ጊዜ በስልክ መነጋገራቸው እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በስልክና በአካል ውይይት መድረጋቸው በሀገራ መካከል ያለው ወዳጅነት መጠናከሩን ያመለክታል ብሏል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዩክሬን፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በሰሜን አፍሪካ፣ በማዕከላዊ እስያ እና በጥቁር ባሕር አካባቢ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን ሚኒስትሮቹ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያዩ ቢሆንም ዋናኛ ጉዳያቸው ግን የሩሲያ እና የዩክሬን የሰላም ንግግርን ዳግም መመለስ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡
ሀለቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ወር ስለሚካሄደውና በሶሪያ ላይ በሚያተኩረው ዓለም አቀፍ የሶሪያ ስብሰባ ዙሪያም ይነጋረገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቱርክ በጦርነት ውስጥ የሚገኙትን ዩክሬን እና ሩሲያን የምትቀርብ ሀገር በመሆኗ ንግግር እንዲጀምሩ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ቱርክ ምንም እንኳን ሩሲያ ዩክሬንን እንደወረረች ብትገልጽም በሩሲያ ላይ የሚሉትን ማዕቀቦች አለመደገፏ ይታወሳል፡፡