በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ሩሲያውያን ወደ ዩክሬን ጦርነት ለመዝመት ጦሩን መቀላቀላቸው ተሰማ
ሩሲያ 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ የጦር አባላት ጥሪ ማቅረቧ ይታወሳል
አዲሶቹ ምልምሎች በ80 ማሰልጠኛ ቦታዎችና ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ላይ ናቸው ተብሏል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የክተት ጥሪ ካወጁ በኋላ ከ 200 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሩሲያ ጦር ሰራዊት ለመቀላቀል መመዝገባቸው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ አስታውቀዋል፡፡
"ከዛሬ ጀምሮ ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ጦር ሰራዊቱ ገብተዋል"ም ነው ያሉት ሚኒስትሩ በቴሌቭዥን መስኮት ቀርበው ባደረጉት ንግግር፡፡
አዲሶቹ ምልምሎች በ80 ማሰልጠኛ ቦታዎችና በስድስት የስልጠና ማዕከላት ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸው ሰርጌ ሾይጉ መናገራቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ 300 ሺህ ለሚሆኑ ተጠባባቂ የጦር አባላት ጥሪ ማቅረቧ አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደፈረንጆቹ መስከረም 21 ቀን ለሀገሪቱ ዜጎች ባደረጉት ንግግር "ሩሲያ የደህንነት ስጋት ከገባት ማንኛውንም መንገድ ትጠቀማለች፣ ይህ ቀልድ አይደለም" ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዱማ በተሰኘው የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ሩሲያ በዩክሬን ለጀመረችው ልዩ ዘመቻ ከዚህ በፊት ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱ ሩሲያዊያን ተጠባባቂ ሀይሎች በዩክሬን የተጀመረውን ዘመቻ እንዲቀላቀሉ ጥሪ ማቅረባቸው ራሺያን ቱዴይ በወቅቱ መዘገቡም አይዘነጋም።
የፑተን ጥሩ በርካታ ሩሲያውያን ዘንዳ ተቀባይነት እንዳገኘ ሁሉ ተቃውሞም ገጥሞታል፡፡ የዘመቻ አዋጁን የተቃወሙ በርካታ ሩሲያውያን ሀገራቸው ጥለው እስከመሰደድም ደርሰዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የክተት ጥሪውን ተከትሎ በየቀኑ ወደ ጆርጂያ የሚሸሹ ሩሲያውያን ቁጥር 10 ሺህ ደርሷል፡፡
የክተት ጥሪን በመቃወምና ጦርነትን በመፍራት ወደ ጎረቤት ሀገራት ከሚሰደዱት በተጨማሪ በክሬምሊን ባለስልጣናት ለእስር የታዳረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን እንዳሉም በርካታ መገናኛ ብዙሃን የመብት ተሟጋች ቡድን መረጃን ዋቢ በማድረግ ሲዘግቡ ተስተውለዋል።
እስካሁን በ32 ከተሞች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረጋቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ግማሾቹ በሞስኮ ውስጥ ይገኛሉ ተብለዋል።
የሩሲያ ድርጊት ከሀገሬው ዜጎች ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድረስ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ቢሆንም፤ የክሬምሊን ባለስልጣናት ግን ድርጊቱ "ህጋዊና አግባብነት ያለው ነው" እያሉ ነው፡፡