ሰሞኑን በታጣቂዎች ከታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 21ዱ መለቀቃቸው ተገለጸ
በኢትዮጵያ በተለይም አማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ 16 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ችግሮች እንደነበሩ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎችም ከ35 ሺ በላይ ተማሪዎች ወደ ቤተሰባቸው አሊያም ወደ ሌሎች አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎችን ለቀው ሄደዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠሩትን ግጭቶች ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተው አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን አስታውሰው፣ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተቋቋመ ቡድንም ወደየዩኒቨርሲቲዎቹ ከመላኩ ባለፈ የፌደራል ፖሊስ የጸጥታ ማስከበር ስራውን እንዲያከናውን መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በየዩኒቨርሲቲዎቹ በተፈጠሩ ግጭቶች እጃቸው አለበት የተባሉ በርካታ ተማዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እርምጃ እንደተወሰደባቸውም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ አንዱ ከሆነው ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት በተከሰተበት ጊዜ በስጋት ምክኒያት ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ሲሄዱ እንደ እርሳቸው ገለጻ 27 ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተዋል፡፡
የታገቱ ተማሪዎችን በሰላማዊ መንገድ ለማስለቀቅ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ከአካባቢው ወጣቶች እና መከላከያ ሰራዊት ጋር ጥረት ሲደረግ የቆየ ሲሆን፣ ከታጋቾቹ 21ዱ በሰላም መለቀቃቸውን አቶ ንጉሱ አስታውቀዋል፡፡ ከተለቀቁት ተማሪዎች 13ቱ ሴቶች ሲሆኑ 8ቱ ወንዶች ናቸው፡፡
አሁን ላይ 6 ተማሪዎች ታግተው እንደሚገኙ ከፖሊስ እና ሌሎች አካላት መረጃ መገኘቱን የገለጹት አቶ ንጉሱ፣ እነርሱንም ለማስለቀቅ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ውጭ የሚለቀቁ ስጋትን የሚያጭሩ መረጃዎች ስህተት በመሆናቸው ሊታረሙ እንደሚገባም ነው ኃላፊው ያሳሰቡት፡፡
በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች ስላለው የእለት ተለት ሁኔታ ከጸጥታ አካላት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ችግሮችን ለማርገብ በመሰራት ላይ እንደሚገኝም የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ኢቢሲ