ለ2 ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በግብጽ አዲስ ሀሳብ ምክኒያት ያለስምምነት ተጠናቀቀ
የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በቀረቡት ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሰፉ ልዩነቶች ባይኖሩም ግብጽ አለመቀበሏን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ፡፡
ለ2 ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረውን የሶስትዮሽ ድርድር በተመለከተ ሚኒስትሩ ዛሬ አመሻሽ ላይ በስካይላይት ሆቴል ተገኝተው ለነበሩ ጋዜጠኞች መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
በድርድሩ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ እና ነገሮችን ለመፍታት ብዙ ርቀት ሄደናል ያሉት ሚኒስትሩ ግብጽ ለመቀበል ባለመፈለጓ አለበለዚያም ዝግጁ ባለመሆኗ ምክንያት ውይይቱ ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ነው የገለጹት።
በድርድሩ ያልነካካነው ጉዳይ ያለም ያሉት ሚኒስትሩ ሙሌትንና የድርቅ አስተዳደርን በተመለከተ ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት ውይይት ሲደረግ ነበርም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአሁን ቀደም ከሱዳን ጋር በደረሰችው ስምምነት መሰረት ባቀረበቸው የሙሌት ሰንጠረዠ ላይ እምብዛም ልዩነት ሳይኖራት ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ሃሳብ ስትለዋወጥ የነበረችው ግብጽ አዲስ የሙሌት ሰንጠረዥ ይዛ መቅረቧን ተናግረዋል፡፡
በሰንጠረዥ መሰረትም ግብጽ የግድቡ ሙሌት ከ12 እስከ 21 ዓመት እንዲሆን ትፈልጋለች፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ በምንም አይነት መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ሳትቀበለው ስለመቅረቷ ነው ሚኒስሩ የተናገሩት፡፡
የህዳሴው ግድብ ከአስዋን ግድብ ጋር እንዲያያዝ ታቀርብ የነበረው ሃሳብ በድጋሚ ቢቀርብም እንደማይሆን ታውቆ ውድቅ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በ4ቱ የድርድር ሂደቶች ያልነካካቸው ጉዳዮች እና ያልተመነዘሩ የቴክኒክ ችግር የሉም ያሉት ሚኒስትሩ ግብጾቹ ዝግጁ ባለመሆናቸው አለበለዚያም ባለመፈለጋቸው ምክንያት ስምምነት ላይ አለመደረሱን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮያጵያ የድርድሮቹን ሂደቶች ለመሪዎቿ እንደምታስታውቅና በመጪው ሰኞ የሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ፣የአሜሪካ የብሄራዊ ባንክ እና የዓለም ባንክ ታዛቢዎች በተገኙበት ውይይቱ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡