ተፈናቃዮቹ በቆቦ፣ ሰሜን ወሎ እና ሰቆጣ ከተሞች መጠለላቸው ተገልጿል
ከአላማጣ እና አካባቢው 29 ሺህ ህዝብ መፈናቀሉ ተገለጸ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት 29 ሺህ ዜጎች ከራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል፡፡
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት ከሆነ ከሰሞኑ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ባገረሸው ግጭት ምክንያት ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡
ተፈናቃዮቹ በቆቦ፣ ሰሜን ወሎ እና ሰቆጣ ከተማ በሚገኙ መጠለያዎች ላይ እንደተጠለሉም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በአካባቢው ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ተጨማሪ ዜጎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የገለጸው ድርጅቱ ለተፈናቃዮች ውሃ፣ ምግብ እና ሌሎች ህይወት ማቆያ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል፡፡
አሁን ላይ ከለጋሽ ተቋማት እና ሀገራት የሚገኘው ድጋፍ እየተሟጠጠ በመሆኑ በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ የሚችለውን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ለተፈናቃዮቹ መጠለያ፣ የሕክምና አገልግሎት እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎችን ማድረግ ይገባል ያለው ድርጅቱ የኢትዮጵያ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚሽን ሰራተኞች ወደ ስፍራው ተሰማርተዋልም ተብሏል፡፡
ተፈናቃዮቹ ከአንድ ሳምንት በፊት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የህወሃት ታጣቂዎች ወደ ራያ እና አላማጣ አካባቢዎች መምጣታቸውን ተከትሎ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ እንደተገደዱ ተገልጿል፡፡
ከተፈናቀሉት 29 ሺህ ዜጎች ውስጥ 70 በመቶዎቹ ህጻናት እና ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ አዛውንቶች እና ታዳጊዎች ናቸው ተብሏል፡፡
በአላማጣ ከተማ የፌደራል የጸጥታ ሀይሎች መግባታቸውን ተከትሎ ተቋርጦ የነበረው ከቆቦ-አላማጣ ትራንስፖርት ዳግም መከፈቱ ተገልጿል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ ክልል ያለው የሀገር መከላከያ ሰሜን እዝ በታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር የተከሰተው፡፡
ለሁለት ዓመት የዘለቀው ይህ ጦርነት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የቆመ ቢሆንም ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ መተግበር አልቻለም፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው የራያ አካባቢ ዳግም ግጭት ተከስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ወታደሮች በአማራ ክልል ባለው ውጊያ እየተሳተፉ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገለጸ
ግጭቱ የተከሰተው የህወሃት ታጣቂዎች ወደ አካባቢዎቹ በመምጣታቸው እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ነዋሪዎችም ለደህንነታቸው በመስጋት ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡
በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተቀሰቀሰ የተባለዉን ግጭት ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት ህወሃት ለአራተኛ ጊዜ ወረራ ፈጽሞብኛል ብሏል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው “በደቡብ ትግራይና በሌሎች በኃይል በተያዙ የትግራይ ግዛቶች እየታየ ያለው ክስተት በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር፤ በህወሓት ወይም ደግሞ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም” ብለዋል።