የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የኤምባሲዎች ስራ መጀመር ትልቅ ምልክት ነው ብለዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ 50 ኤምባሲዎች በድጋሚ በኪይቭ ስራ መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡
ምንም እንኳን ሀገራቸው በጦርነት ውስጥ ብትሆንም፤ የዲፕሎማቲክ ተቋማት ስራ መጀመራቸው ትልቅ ድል መሆኑንም ነው ዘለንስኪ የተናገሩት፡፡ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ከገቡ አራት ወር እየሞላቸው ሲሆን ሁለቱም ወገኖች ድል እየተቀዳጁ መሆኑን እየገለጹ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ደግሞ አሁን ላይ 50 ኤምባሲዎች አቋርጠውት የነበረውን ስራ መጀመራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህ የውጭ ሚሽኖች ዳግም ስራ መጀመር በሀገሪቱ ድል አድራጊነት ላይ ያለ እምነት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የኤምባሲዎቹ ስራ መጀመር ተግባራዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ትርጉሙ ትልቅ መሆኑንም ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አስታውቀዋል፡፡ ስራ አቁመው የነበሩ ኤምባሲዎች ተመልሰው በመዲናዋ ኪይቭ ስራ መጀመራቸው በድል እምነት እንዳላቸው ምልክት መሆኑንም ገልጸዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
በዩክሬን የነበረው የሕንድ ኤምባሲ በጊዜያዊነት ከፖላንድ ውጭ ሲሰራ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ግን ወደ ኪይቭ ተመልሶ ስራ መጀመሩን የሕንድ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡
የሕንድ ኤምባሲ በዩክሬን በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማዋ ዋርሶ ተዘዋውሮ የነበረ ቢሆንም፤ ከፖላንድ ውጭም ሲሰራ ነበር ተብሏል፡፡ ሕንድ በዩክሬን የነበሩ 22 ሺ 500 ዜጎቿን ማስወጣቷም የሚታወስ ነው፡፡
አሜሪካ በበኩሏ ለሶስት ወራት አቋርጣው የነበረውን የዩክሬን ኤምባሲዋን በፈረንጆቹ ግንቦት 18 ቀን ስራ አስጀምራለች፡፡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ኤምባሲው ከኪቭ ወደ ሌላ ቦታ በተዘዋወረበት ጊዜም ቢሆን ሀገራው ከዩክሬን ጎን እንደነበረች ገልጸው ነበር፡፡
ቃል አቀባዩ አሁንም አሜሪካ ከዩክሬን መንግስት እና ሕዝብ ጎን መቆሟን ማረጋገጣቸው ተዘግቧል፡፡ በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል የተጀመረው ጦርነት ነገ አራት ወር ወይም 120 ቀን ይሞላዋል፡፡