ምዕራባዊያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ መስጠታቸውን እንዲያቆሙ ሩሲያ አስጠንቅቃለች
ሩሲያ ከአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን የተለገሱ የጦር መሳሪያዎችን ማውደሟን አስታወቀች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች 102 ቀናት ሆኖታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ6 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ዜጎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ሲሰደዱ 20 በመቶ የዩክሬን ክፍልም በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ወድቋል።
ጦርነቱን ተከትሎም አውሮፓ ህብረት፣አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሲሆን፤ ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በመለገስ ላይ ሲሆኑ፤ ሩሲያም የተለገሱትን የጦር መሳሪያዎች በማውደም ላይ መሆኗን ገልጻለች።
ከሰሞኑ ከአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የተለገሱ የጦር ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ማውደሟን የሀገሪቱ ዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እንዳይለግሱ አሳስበው ልገሳቸውን ከቀጠሉ ግን እርምጃ መውሰዴን እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።
በተለይም ምእራባዊያን ሀገራት ረጅም ርቀት ተወንጫፍ ሚሳኤሎችን እንዳይለግሱ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ ደህንነቷን ለመጠበቅ ስትል እርምጃ ትወስዳለች ብለዋል።
አሜሪካ፣ ስፔን እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ለዩክሬን ሚሳኤሎች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለግሰዋል ተብሏል።
እንደ ሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ከሆነ ምዕራባዊያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ በመለገስ ጦርነቱን የማራዘም እቅድ እንዳላቸው ተገልጿል።