ከሟቾቹ መካከል 2ቱ ህጻናት ናቸው
በአሶሳ ከተማ አስተዳደር አንድ ተጠርጣሪ ግለሰብ 9 ሰዎች ላይ ባደረሰው የስለት ጥቃት የ4ት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ጥቃቱ በተለምዶ ጎንድል ተብሎ በሚጠራው የከተማው አካባቢ ጥር 21 /2012 ዓ/ም ረፋድ ላይ የተፈጸመ ሲሆን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 5 ሰዎች በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ግለሰቡ ጩቤ እና ጦር በመያዝ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ኮሚሽነር ሙሀመድ ሀመደኒል የጥቃቱ ተጎጂ የሆኑ 2 ህጻናትና 2 ወጣቶች ህይዎታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪ ግለሰቡ የጸጥታ አካለት ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር ውሏል ያሉት ኮሚሽነሩ ተጠርጣሪው የአእምሮ ተማሚ መሆን አለመሆኑም በህክምና በማረጋገጥ አስፈላጊው ምርመራ እንደሚደረግበትም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ነጋ ጃራ በበኩላቸው ግለሰቡ ሰብዓዊነት በጎደለው ድርጊቱ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ህጻናት እና ሴቶች ላይ ጉዳት በማድረስ ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጎ በመሽሽ ላይ እያለ ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም መሰል የወንጀል ድርጊቶች በዜጎች ላይ እንዳይደር ፖሊስ በሚያደርገው የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ጥቆማ እና ድጋፍ እንዲያደርግም ምክትል ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን የተመኙት ኮሚሽነር መሀመድ በከተማዋ ጫትና ተዛማጅ ሱስ አስያዥ እጾች በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል አዕምሮ እና ስነ ምግባር ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ለመቅረፍ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚሰራ ስለመናገራቸው የክልሉ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡