
ዘለንስኪ 198 ሺህ የሩሲያ ወታሮች በጦርነቱ ተገድለዋል ብለዋል
ፕሬዝዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት የሞቱ የዩክሬን ወታሮች ቁጥር 43 ሺህ መድረሱን አስታወቁ።
ዘለንስኪ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ባጋሩት ጽሁፍ፤ ከሞቱት በተጨማሪ 370 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች ቆስለዋል ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የቆሰሉ ወታሮች ይገኙበታል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ አክለውም በጦርነቱ 198 ሺሀ የሩሲያ ወታደሮች መሞታቸውን እና 550 ሺህ ወታደሮች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
ሁለቱም ወገን ማለትም ሞስኮ እና ኪቭ በተለያዩ ጊዜያት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ያደረሱትን ጉዳት በአሃዝ አስደግፈው የሚያቀርቡ ሲሆን፤ በራሳቸው ወገን ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ግን ለማረጋገጥ ፍቃደኛ አይደሉም።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ይፋ ያደረጉት አዲስ አሃዝ በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆቹ 2024 ዓመት የሚሞቱ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ እንዳሳየ ያመላክታል።
ዘለንስኪ ባሳለፍነው የካቲት ወር ላይ ከሩሲያ ጋር እየተደረገ ባለው ጦርነት የሞቱ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር 31 ሺህ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በወቅቱ ባወጡት መረጃ በጦርነቱ 70 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች መሞታቸውን ሲገልጹ 120 ሺህ ያህሉ ደግሞ መቁሰላቸውን ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
አንድ ሺህ ቀን ያለፈው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት በርካታ አዳዲስ ነገሮችን እያስተናገደ ይገኛል።
ዩክሬን በየጊዜው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገች ሲሆን 100 ሺህ ያህል ወታደሮቿ ከጦር ግምባር ጠፍተዋል ተብሏል፡፡
የዩክሬን ወታደሮች ሳያስፈቅዱ ከጦር ግምባር መጥፋት፣ የመዋጋት ፍላጎት ማነስ፣ ለፈቃድ በሚል ከወጡ በኋላ በዛው መጥፋት እና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች አጋጥሟቸዋል።
የዩክሬን ጦር በዚህ ምክንያት እየተፈተነ ነው የተባለ ሲሆን ክስተቱ ደግሞ ለሩሲያ እንደ ትልቅ አጋጣሚ ተወስዷል።
የሩሲያ ጦር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ ነው የተባለ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በዩክሬን በኩል ያለው የመከላከል አቅም አነስተኛ በመሆኑ ነው ተብሏል።