ባለ 5 ኮከቡ የድመቶች ሆቴል
የድመቶች ጌቶች ድመቶቻቸው በዚህ ቅንጡ ሆቴል እንዲገለገሉ ከወራት ፣ አንዳንዴም ከዓመታት በፊት ቦታ መያዝ ይጠበቅባቸዋል
በሆቴሉ የሚስተናገዱ ድመቶች የቅንጦት ምግቦች እና ማሳጅ ጭምር ይገለገላሉ
ፍርቱና በሆነችው ዓለም ፣ ለንጽጽር የሚከብዱ ፣ በየጊዜው ብዙ አዳዲስ እና አስደናቂ ወሬዎች ይሰማሉ፡፡
ከተለያዩ ሰዎች በኢንተርኔት ላይ በተሰበሰበ አስተያየት መሰረት ከብሪታንያ ውጭ መጓዙ የሚፈልጉ አብዛኛው ቤተሰቦች ድመቶቻቸውን በብቃት እና በጥንቃቄ ማስተናገድ የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲኖሩ ይሻሉ፡፡
ይህን የደንበኞችን መሻት መሰረት በማድረግ በብሪታኒያ የተከፈተው ‘ሎንግ ክሮፍት’ ባለ 5 ኮከብ የድመቶች ሆቴል የብዙ ባለድመቶችን ጭንቀት ስለማቅለሉ ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ድመቶቹ በሆቴል የሚቆዩበት ጊዜ ደግሞ ከሁለት ቀናት እስከ ሳምንታት ፣ አንዳንዴም እስከ ወራቶች ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት የሆቴሉ አስተዳደር ለድመቶች ባለቤቶች በቪዲዮ እና በፎቶግራፎች አማካይነት ስለ ጤናቸው እና ስለ አጠቃላይ ተዝናኖታቸው መረጃ ያደርሳል፡፡
ለድመቶቹ ቆይታ የሚከፈለው ክፍያ እንደሚሰጣቸው አገልግሎት እና ከሆቴል ይለያያል፡፡ ይሁንና የአንድ ምሽት ክፍያ ከ 10 ፓውንድ እስከ 24 ፓውንድ ይደርሳል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2010 የተመሰረተው እና 25 ቅርንጫፎች ያሉት “ሎንግ ክሮፍት” ሆቴሎች ግሩፕ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል የሆኑት ሉሲ “ድመቶችን እንደ እንግዳ ማስተናገድ ከሰዎች ጋር ከመግባባት ያነሰ አይደለም ፤ ለሁለቱም ፍላጎቶቻቸው መሟላት አለባቸው” ብለዋል፡፡
ሉሲ እንዳለችው የድመት ሆቴሎች በድመት ምግቦች ልዩ ሙያ ያለው ሼፍ ላያስፈልጋቸው ይችላልል ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ምግብ በተናጠል ለእያንዳንዱ እንግዳ ድመት ተስማሚ መሆኑን ለማረጋገጥ የምግብ ጥናት ባለሙያዎችን በማማከር ነው የሚዘጋለው፡፡
በብዛት ለድመቶች እንደ ዋና ምግብ የሚቀርቡ ተስማሚ ምግቦች የቱና ፣ የዶሮ እና ሽሪምፕ ቁርጥራጮችን ያጠቃልላል፡፡ ቀለል ያሉ ልዩ የብስኩት አይነቶች ደግሞ ለብ ባለ ወተት ከዋና የምግብ ጊዜዎች ውጭ ይቀርቡላቸዋል፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት ድመቶች ምግብን በተመለከተ በጣም መራጮች ናቸው፡፡ የድመቶች የምግብ ምርጫ እንደ ድመቱ/ቷ ዓይነት ፣ ዕድሜ ፣ ክብደት እና ዝርያ ይለያያል፡፡
ባለ 5 ኮከቡ ሆቴል ውስጥ በኃላፊነት የምትሰራው ሉሲ “የድመቶችን ክፍል የሙቀት መጠን ሁል ጊዜ እንቆጣጠራለን ፤ የአልጋዎቻቸው አንሶላዎች እና የብርድ ልብሶቻቸውንም ንጽህና እና ምቾት እንከታተላለን” ስትል ገልጻለች፡፡
ዘና የሚሉበት እና ጌሞችን የሚጫወቱበት ምቹ ቦታ ከመዘጋጀቱ በተጨማሪ የሙሉ አካል እጥበት እና የማሳጅ አገልግሎትም እንደሚሰጣቸው ነው ሉሲ የተናገረችው፡፡
ድመቶች በሆቴል ቆይታቸው ሕክምናን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችንም እንደሚያገኙ ነው ዘገባው የሚያመለክተው፡፡
ይህ በፍርቱናዎች የተሞላችው ዓለም ሌላ እውነታ ነው፡፡