ህብረቱ ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የበይነ መረብ ንግግር ለማድረግ ያቀረቡትን ጥያቄ መቀበሉን አስታውቋል
የአፍሪካ ህብረት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀበለ፡፡
ህብረቱ፤ ዜሌንስኪ አባላቱን በበይነ መረብ አግኝተው ንግግር እንዲያደርጉ ፈቅዷል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በህብረቱ ንግግር ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አቅርበው ነበረ፡፡ ከወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ለሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ደውለው በተነጋሩባቸው ጊዜያት ሁሉ ንግግር ለማድረግ ጠይቀዋል፡፡
ማኪ ሳል ጥያቄውን መቀበላቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል፡፡
ማኪ ሳል በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግብዣ ዛሬ ሃሙስ ወደ ሩሲያ ያቀኑ ሲሆን ነገ አርብ በሪዞርት ከተማዋ ሶቺ ፑቲንን እንደሚያገኙና ወደ አፍሪካ መግባት ሲገባቸው በዩክሬን ወደቦች ላይ ስለቀሩ የምግብ እና የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ምርቶች ጉዳይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከአሁን ቀደም በተለያዩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ምክር ቤቶች የበይነ መረብ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡
ኬንያን መሰል አንዳንድ የአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት ሩሲያ በዩክሬን ጦሯን ማዝመቷን በይፋ ቢቃወሙም ብዙዎቹ ግን እስካሁን አቋማቸውን በአደባባይ አላንጸባረቁም፡፡ ጦርነቱ እንዲቆምና ሰላማዊ መፍትሄዎች እንዲፈለጉ ከመጠየቅም ውጪ በገሃድ ሩሲያን አውግዞ እርምጃዎችን የወሰደ ሃገርም የለም፤ ምንም እንኳን አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አጥብቀው የሚፈልጉት ጉዳይ ቢሆንም፡፡
በአፍሪካ ህብረት ንግግር የሚያደርጉበትን ፈቃድ ያገኙት ዜሌንስኪም ለአባል ሃገራቱ መሪዎች ስለ ጦርነቱ በመግለጽ የሃገራቱን አቋም ለማወቅና ድጋፍ ለማሰባበስብ ያስባሉ፡፡
ሆኖም ብዙዎቹ የህብረቱ አባል ሃገራት ከሩሲያ ጋር በተለይም በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ተከትሎ ይህን ያህል የተለየ አቋምን ያንጸባርቃሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡